በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

1489

ጥር 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ገለፀ።

“በኤርትራ ስደተኞች ላይ ችግር እንደደረሰ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ እውነታውን ያላገናዘበ ነው” ብሏል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ትናንት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ከተመድ ልዑካን ቡድን ጋር በስፍራው ተገኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ የተሻለ የህግ ማዕቀፍ ቀርጻ ስደተኞች በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ታደርጋለች።

ባለፉት ሶስት ወራትም የስደተኛ ጣቢያዎችን ለማሻሻል በርካታ ተግባራት መከናወናቸወን አቶ ተስፋሁን አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ በኤርትራ ስደተኞች ላይ ችግር እንደደረሰ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ እውነታውን ያላገናዘበ መሆኑን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው “ቦታው ላይ ተገኝቶ ስደተኞቹን መጎብኘት ያለውን እውነታ ለመረዳት ያስችላል” ብለዋል።

የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞችን ሁኔታ በትኩረት እንደሚመለከት ገልፀዋል።

በአንዳንድ አካላት የሚናፈሱ ወሬዎች ተጨባጭነታቸው ያልተረጋገጠ መሆኑን አመልክተው፤ ችግር አጋጥሞ ከሆነም መንግስት የማጣራት ስራ በመስራት ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ስደተኞችን ተቀብላ ታስተናግዳለች።

ከእነዚህ ውስጥ 100 ሺህ የሚሆኑት ኤርትራዊያን ስደተኞች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 46 ሺህ የሚሆኑት በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ትናንት የጎበኙት በርካታ የኤርትራ ስደተኞች የያዘውን መጠለያ ጣቢያ ነው።