በአፋር የበረሃ አንበጣን ለመቆጣጠር በሄሊኮፕተር የታገዘ ቅኝትና አሰሳ እየተካሄደ ነው

1556

ሰመራ፣ ጥር 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የተከሰተን የበረሃ አንበጣ ለመቆጣጠር በሄሊኮፕተር የታገዘ ቅኝትና አሰሳ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ እርሻ፣ አርብቶ አደርና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ እስካሁን የአንበጣ መንጋው ያረፈበትን ጨምሮ ከ91 ሺህ ሄክታር በላይ ቁጥቋጦና ግጦሽ ሳር መጎዳቱ ተነግሯል።

በቢሮው የበረሃ አንበጣ መከላከል ግብረ-ሃይል አስተባባሪ ዶክተር አያሌው ሹመት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከጂቡቲና ሶማሌያ በኩል አቋርጦ የገባ የበረሃ አንበጣ ከጥር 9 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ በ16 ወረዳዎች ተከስቷል።

ዱብቲ፣ አሳኢታና አፋምቦ ወረዳን ጨምሮ በፈንቲ-ረሱ ዞን በተለያዩ ሰብል አብቃይ ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን ጠቅሰዋል።

የበረሃ አንበጣው በእንስሳት መኖና በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ በባህላዊ መንገድ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና የበረሃ አንበጣው በተለያዩ አካባቢዎች ተደብቆ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ ቢሮው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አመልክተዋል።

ከሚኒስቴሩ በተመደበ አንድ ሄሊኮፕተር በመታገዝ በ16 ወረዳዎች ቅኝትና አሰሳ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረው፤ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ በሄሊኮፕተር በመታገዘ 415 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ ቅኝትና አሰሳ መካሄዱን ተናግረዋል።

በቅኝቱ አንበጣ ያረፈበትን ጨምሮ ከ91ሺህ ሄክታር በላይ ቁጥቋጦና ግጦሽ ሳር በመንጋው ጉዳት እንደደረሰበት አመልክተዋል።

በተለይም በአንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተ የአንበጣ መንጋ እንቁላል ለመጣል ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ከሄሊኮፕተር በተጨማሪ በሰውና በተሽከርካሪ የታገዘ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአፋር ክልል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በሚከሰት የአንበጣ መንጋ በሰብልና ግጦሽ ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።