የምዕራብ ሸዋ ዞን ዓመታዊ የባህል ስፖርቶች ውድድር ተጀመረ

86

አምቦ ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን 21ኛው ዓመታዊ የባህል ስፖርቶች ውድድር ዛሬ በአምቦ ከተማ ተጀመረ።

በውድድሩ በሁለቱም ጾታ 22 ወረዳዎችን የወከሉ 218 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረፌራ ቱሉ  በወቅቱ እንደገለጹት ውድድሩ በገበጣ ፣ ቦብ ፣ ኩርቦ ፣ ገና፣ቀስት፣ ሻህ፣ የፈረስ ሸርጥና ጉግስ የባህል ስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ነው።

ውድድሩ በዚህ ወር መጨረሻ በለገ ጣፎ ከተማ  በሚካሄደው  ክልል አቀፍ  የባህል  ስፖርቶች  ውድድርና 

ፌስቲቫል ላይ ዞኑን ወክለው የሚሰለፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የምእራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቶለሳ አጀማ  በበኩላቸው የአምቦ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች 

ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ውድድሩን በመከታተል  ስፖርተኞችን  እንዲደግፉና  እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውድድሩ መክፈቻ በተደረገ የገና ጫወታ የድሬ ኢንጪኒ ወረዳ ከቶኬ ኩታዬ  ወረዳ  ያለ ውጤት ተለያይተዋል።

ውድድሩ እስከ ጥር 28 ቀን 2013 ዓም እንደሚቆይ የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም