ህገ-ወጥ ደላሎች የወጣቶችን ህይወት እያበላሹ ነው… ለህገ-ወጥ ስደት የተጋለጡ ወጣቶቹ

140

መተማ  ጥር 23/2013 (ኢዜአ) ህገ-ወጥ ስደትን በሚያበረታቱ ደላሎች የተሰጠን ያልተጨበጠ የኢኮኖሚ ተስፋ ለችግር አጋልጦናል ሲሉ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት የሞከሩ ወጣቶች ገለፁ።

በመተማ በኩል ወደ ሱዳን የሚደረግ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በዚህ ዓመት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱም ተመልክቷል።

በመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ትዕግስት ዳና በ2010 ዓ.ም ከደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በህገ-ወጥ መንገድ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ለመውጣት 15 ሺህ ብር ከፍላ እዚህ መድረሷን ታስታውሳለች፡፡

ይሁን እንጂ ካሰበችው መድረስ ይቅርና ለከፍተኛ እንግልት በመዳረግ በማታውቀው ቦታ ከቤተሰቦቿ ጋር ከነበረችበት የኑሮ ደረጃ ባነሰ መልኩ ት እየሠራች መሆኗን ገልጻለች።

በወቅቱ ከቤተሰቦቿ ተቀብላ ለደላላና ለትራንስፖርት ወጭ ያደረገችው ገንዘብም በትውልድ ቀየዋ አነስተኛ ስራ የሚያስጀምራት እንደነበር አስታውሳ፤ በህገ-ወጥ ደላሎች አጉል ተስፋ ወላጆቿን ለእዳ እሷንም ለችግር ማጋለጧን ተናግራለች፡፡

''ወደ ትውልድ አካባቢዬ ለመመለስ ባስብም ይዤ የምመለሰው ገንዘብ የሌለኝ በመሆኑ እስከ አሁን አልተመለስኩም'' ብላለች።

''ደላሎች ሰርተሽ ሃብታም ትሆኛለሽ፤ ትለወጫለኝ ቤተሰብሽን ትረጃለሽ ብለው የሰጡኝ ተስፋ መና ቀርቶ የህይወቴን እጣ ፋንታ አበላሽቸዋለሁ'' ስትል በፀፀት ገልፃለች።

ከሰሜን ወሎ ዞን ''ከትውልድ አካባቢዬ ወደ ሱዳን ለመሻገር የወጣሁት በ2009 ዓ.ም መስከረም ወር ሲሆን ሱዳን የተወሰነ ሰርቼ ወደ አረብ ሃገር ለመሻገር እቅድ ነበረኝ'' ያለችው ደግሞ ወጣት ሃና መንበሩ ናት።

በሰው ሀገር ሰርታ ራሷንና ቤተሰቦቿን በኢኮኖሚ ለመለወጥ በማሰብ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ብትመጣም ያሰበቸውን ማሳካት እንዳልቻለች በሃዘን ትናገራለች።

የትምህርት ቤት ጓደኞቿ በዚህ አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ የተናገረችው ወጣቷ ስለ ስደት የህልም እንጀራ የነገሯትን ግለሰቦች ስትረግም እንደምትኖር ገልጻለች።

''ሱዳን ድረስ እኔ አደርስሻለሁ ከሱዳን በኋላ ደግሞ አረብ ሃገር ሚያሻግርሽ ሰው አገናኝሻለሁ” ብሎ ከቤተሰብ በሌለ አቅማቸው 10 ሺህ ብር ተቀብዬ እንድወጣ ያደረገኝ ሰው መተማ ዮሃንስ ከተማ ካደረሰኝ በኋላ የያዝኩት ብር ሲያልቅ ጥሎኝ ጠፋ'' ስትል ገልፃለች።

በጊዜው የቀን ጨለማ እንደሆነባት አታውሳ ወደ ቤተሰቦቿ ለመመለስ ብታስብም ከቤተሰብ መመለሻ ገንዘብ የሌላት በመሆኑ ወደ ማትፈልገውና ህይወቷን አደጋ ላይ በሚጥል ሴተኛ አዳሪነት ህይወት እንድትገባ እንዳስገደዳት ተናግራለች።

''አሁን ያ ሁሉ ህልሜ መክኗል የምኖረውም ህይዎቴን አደጋ ላይ ጥዬ ነው ያለችው ወጣቷ፤ ሌሎች የእኛ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው ደላሎችን መስማት የለባቸውም'' ብላለች።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህፃናት ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር የመንግስት አየነው በበኩላቸው በህገ-ወጥ መንገድ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ለመውጣት የሚሞክሩት ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት 900 የሚሆኑ ወጣቶች ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘው ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅው፤ ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከሦስት እጥፍ በላይ ማደጉን ገልፀዋል።

ታዳጊ ወጣቶቹ ለህገ-ወጥ ደላሎችና ለትራንስፖርት ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ በመክፈል እስከ መተማ የሚደርሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ወጣቶቹ በመንገድ ላይ ''ረሃብና ጥም፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ድብደባ፣ ዘረፋና ሌሎች ጥቃቶች እየደረሰባቸው ነው'' ብለዋል።

በፀጥታ አካላት በሚያዙበት ወቅትም የማረፊያ ክፍል ባለመኖሩ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጫና ማሳደሩን አመልክተዋል።

በዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የቡድን መሪ አቶ ምርኩዝ ዘመነ በኩላቸው እንደተናገሩት ህገ-ወጥ ስደት በዞኑ ላይ ኦኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ከማሳደሩም በላይ ዜጎች ለአካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እየተዳረጉ ነው።

“ወጣቶቹ የተሻለ ስራና ገቢ ፍለጋ በሚል ህገ-ወጥ ደላሎች በሚነግሯቸው የፈጠራ ተስፋ ከቀያቸው በመውጣት ለእንግልትና ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ”ብለዋል ።

በመሆኑም ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ መሰራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ ደላሎችን በመጠቆምና ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግም ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም