የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ በዓል በእንጅባራ እየተከበረ ነው

130

እንጅባራ ጥር 23 /2013 (ኢዜአ)-በአዊ ዞን 81ኛው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ በዓል ዛሬ በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ዘውዲቱ ወርቁ በወቅቱ እንደገለጹት በዓሉን ትወፊቱን በጠበቀ መልኩ በማክበር ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋልና ለዓለም ማህብረተሰብ ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው።

በዓሉ በፈረስ ጉግስ፣ በስርጥና በሌሎችም ውድድሮች እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ካለፉት አራት አመት ወዲህ በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን አመልከተዋል።

በዓሉ ቀደም ሲል በጣሊያን ወረራ ወቅት ፈረስና ፈረሰኞች ያበረከቱትን አስተዋጻ ለማስታወስ ይከበር እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይም ማህበሩ 78ኛ ዓመቱን ካከበረበት ካለፉት አራት አመት ጀምሮ አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማደረገ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በእንጅባራ ከተማ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዛሬ እየተከበረ ባለው የማህበሩ በዓል ላይ ከፌደራልና ክልል የተውጣጡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የስራ ሀላፊዎች፣ ህብረተሰቡና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ከ53ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም