የጌዴኦ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በይርጋጨፌ ወረዳ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

86

ዲላ ጥር 22/2013 ኢዜአ) 18ኛው የጌዴኦ ዞን የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በይርጋጨፌ ወረዳ አጠቃላይ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ።

በይርጋጨፈ ወረዳ ስድስት  ዋንጫዎችን በመውሰድ አጠቅላይ አሸናፈ ሲሆን በስፖርታዊ ጨዋነት ደግሞ ቡሌ ወረዳ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በዲላ ስታዲዬም ሲካሄድ የሰነበተው  ውድድርና ፌስቲቫል ሲጠናቀቅ የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ሃላፊ አቶ የምስራች ዳካ እንዳሉት ከዞኑ ስምንት  ወረዳዎችና አራት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 300 የሚደርሱ ስፖርተኞች  ተሳትፈዋል።

ኮርቦ ትግል፣ ገበጣናን ጨምሮ 10 የባህላዊ ስፖርቶች ውድድር የተደረገባቸው ሲሆን የተለያዩ ባህላዊ ትሪቶችም መቀርባቸውን ገልጸዋል።

ውድድሩ ማህበራዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ ተተኪ ስፖርተኞች መለየት የተቻለበት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ዞኑን ወክለው በክልል ደረጃ የሚወዳደሩ ስፖርተኞች መመልመላቸውንም አስረድተዋል።

ባህላዊ ስፖርቶች እንዲተዋወቁ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ስፖርተኞች ተግተው መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ የእለቱ የክብር እንግዳ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ለምለም ከበደ ናቸው።

ዞኑን ወክለው በክልል ደረጃ እንዲወዳደሩ የተመረጡ ስፖርተኞችም ስፖርታዊ ጨዋነትን ከማክበር ባለፈ የተሻለ ሰርተው ውጤት ማስመዝገብ ንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዮሰፍ ማሩ  ዝግጅቱ የተሳካ እንዲሆን አሰተዋጽኦ   ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በዞኑ በባህላዊ ስፖርቶች ዘርፍ የሚስተዋለውን የማዘውተርያ ስፍራ፣ የአሰልጣኞችና የዳኞች እጥረት ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም