"በገበታ ለሀገር" ፕሮጀክቶች ዘመነኛና ከብክለት የፀዳ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ለመገንባት ዝግጅት ጀምሬያለሁ - ኢትዮ-ቴሌኮም

120

አዲስ አበባ፣ ጥር 22/2013 ( ኢዜአ) "በገበታ ለሀገር" ፕሮጀክቶች ዘመናዊና ከብክለት የፀዳ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ለመገንባት ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሩን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ።

ከቢሮ እስከ ሀገር በሚል እሳቤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተቀረጸው "የገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ወንጪ እና በደቡብ የኮይሻ አካባቢዎችን የማልማት ውጥን ይዟል።

ፕሮጀክቶቹን እውን ለማድረግ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ያሉበት ኮሚቴም ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ደግሞ ፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጓቸውን የቴክኖሎጂ መረብ ትስስር የሚከውን ይሆናል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ያሉበት ቡድን ትናንት በወንጪ ሃይቅ የመስክ ምልከታ አከናውኗል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ለፕሮጀክቱ ከሰጠው የ500 ሚሊዮን ብር ገንዘብ በተጨማሪ በሚለሙት አካባቢዎች ዘመናዊ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሯል።

የተቋሙ የቴክኒክ ቡድን ቀደም ብሎ ወደ ወንጪ ሀይቅ በመሄድ አስፈላጊውን ጥናት ካደረገ በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዲዛይን ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የተቋሙ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጉብኝትም የተቀረጸው ዲዛይን ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያለው ትስስር ምን እንደሚመስል በአካል ለመመልከት መሆኑን አንስተዋል።

በዲዛይኑ መሰረት በአካባቢው ሕዝባዊ 'ዋይፋይ' ጨምሮ ዘመናዊ የኢንተርኔት አገልግሎቶች እንደሚኖሩ ነው የገለጹት።

የሚዘረጋው የቴሌኮም አገልግሎት የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ሳይጎዳ እንደሚገነባ ጠቁመው፤ ከፀሃይ ብርሃን ሃይል በመጠቀም አገልግሎቱን ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል።

በቁርጠኝነት ከሰራን ምንም ነገር ማድረግ እንደምንችል "የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት" ትምህርት ሰጥቶናል ሲሉም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተናገሩት

በመሆኑም አይቻልም፣ አቅም የለንም ከሚል እሳቤ ወጥተን ሃብቶቻችንን መጠቀም አለብን ብለዋል።

ለዚህም ተጀምረው በአጭር ጊዜ በስኬት የተጠናቀቁ  በርካታ ፕሮጀክቶች ምስክር መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ነገን በተስፋ እንዲጠብቁ እንዳደረጋቸው ለኢዜአ ገልፀዋል።

በአካባቢው በጀልባ መቅዘፍ ስራ አምስት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት አቶ ባይሳ አረጉ፤ የፕሮጀክቱን እውን መሆን በቴሌቪዥን እንደሰሙ ገልጸው፤ የማልማት ስራው እስኪጀመር በተስፋ እየጠበቁ መሆኑን አክለዋል።

መንግስት የተረሳውን የወንጪ ሃይቅ ማስታወሱ ደስታ እንደፈጠረባቸውም ነው የተናገሩት።

የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቀጣይ ወደ ጎርጎራና ኮይሻ አካባቢዎች በማቅናት መሰል የመስክ ምልከታ እንደሚያደርጉ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም