የህወሓት የጥፋት ቡድን የፈጸመውን ወንጀል የሚያሳይ የሶስት ወራት የምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

75

ጥር 21/2013 (ኢዜአ) የህወሓት የጥፋት ኃይል የፈጸማቸውን የአገር ክህደት ወንጀሎች የሚያሳይ የሶስት ወራት የምርመራ ውጤት ይፋ ሆኗል።

የምርመራ ውጤቱ ይፋ የሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው።

በሪፖርቱ በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ከተፈፀመው ጥቃትጋር በተያያዘ 349 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶ 124ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ምርመራው በመቐለ፣ ማይካድራ እና ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የደረሰውን የሠብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፌዴራል መንግስቱን አደጋ ላይ ለመጣል የተሄደበት ርቀት፣ በአገር ክህደትና ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ ለመጣል የተሰማሩ የጁንታው አመራር አካላት የፈጸሙትን እኩይ ጥፋት ለመገንዘብ ላለፉት ሶስት ወራት የተቀናጀ ግብረ ኃይል በማቋቋም ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል።

ጡረታ የወጡ እና የጸጥታ ተቋማትን ከድተው አገር ለማፍረስ የተሰማሩ 253 የጥፋት ቡድኑ አባላት በጥፋት ተልዕኮው ላይ ተሳታፊ እንደነበሩም በምርመራ ተረጋግጧል።

ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ እንዳሉት የህወሓት ቡድን ካለፈው ጥቅምት 24 በፊት አገር ለማፍረስ በርካታ ዝግጅቶች ሲያከናውን ቆይቷል።

ለዚሁ ዓላማው በበጀት፣ በሰው ኃይል ስልጠናና በመሳሪያ አቅርቦት የተደራጀ የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንዶ ወይም የመከላከያ ካውንስል የሚል መዋቅር ዘርግቶ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ እንደነበረም በምርመራ መረጋገጡን አንስተዋል።

የመከላከያ ሰራዊትን ለመዋጋት በሚያስችል ደረጃ በየዓመቱ ከ5 ሺህ በላይ ልዩ ኃይል በማሰልጠን ወደ ጦርነት መግባቱንም አውስተዋል።

ጦርነቱን በሶስት ወራት ለማጠናቀቅ በቂ ፋይናንስ በመመደብና ከ170 ሺህ በላይ የሚሊሻና ልዩ ኃይል በማሰልጠን ወደ ጥፋት ተግባር መግባቱ በምርመራ እንደተረጋገጠም አስረድተዋል።

ቡድኑ የትግራይ መከላከያ ኮማንዶ ወይንም የመከላከያ ካውንስል በሚል 8 ዕዞችና 23 ሬጅመንቶች ያሏቸውና በጡረታ የተሰናበቱ የጦር መኮንኖች የሚመሯቸው የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መስርቶ እንደነበር በምርመራ መረጋገጡን አመላክተዋል።

ምሽጎች በመቆፈርና በመገንባት፣ መንገድ በመቁረጥና የጦር መሳሪያ በማጓጓዝ መሶቦ ሲሚንቶን፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ መስፍን ኢንጂነሪንግና ሌሎች የኢፈርት ኩባንያ አካል የሆኑ ተቋማት የየራሳቸው ሚና እንደነበራቸውም ተረጋግጧል ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በጡረታ የተሰናበቱትን ጨምሮ የፖለቲካ አመራር፣ የጦር መኮንንና የፓርቲ አመራር የነበሩ 349 ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወጥቶባቸው 124ቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ቀሪዎቹ መደምሰሳቸውን ገልፀዋል።

ከተጠሪጣሪዎቹ 96ቱ ቁልፍ የህወሓት አመራሮች ዒ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር በአገረ መንግስቱ ላይ ከፍተኛ ሽብር ሲጠነስሱና ስምሪት ሲሰጡ እንደነበረም አብራርተዋል።

የጥፋት ቡድኑ አገር ለማፍረስ ተዘጋጅቶ እንደነበር በመኖሪያ ቤቶች፣ በጽህፈት ቤቶችና በቢሮዎች ውስጥ በምርመራ ሂደቱ ከተሰበሰቡ ከ680 በላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

የዚህ እኩይ ዓላማ ፈጻሚዎች በማይካድራ ንጹኃን የአማራ ተወላጆችን በገጀራ፣ በፈራድ፣ በካራ እና ለማምለጥ የሞከሩትን ደግሞ በጥይት በመምታት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ማካሄዳቸው በምርመራ እንደተረጋገጠ በመግለጫው ተነስቷል።  

ከዚህ ጋር በተያያዘም 256 ተጠርጣሪዎች በማይካድራ የንጹኃን ጅምላ ጭፍጨፋ ላይ ተሳታፊ እንደነበሩም ተጠቁሟል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 110 በሚሆኑት ላይ ሙሉ መረጃ መሰብሰቡን፣ 137 የሚሆኑት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለው በ37ቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የተጠናቀረ ሙሉ ምርመራ መካሄዱ ተገልጿል።

በዚህም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተደረገ ሳይንሳዊ የተደራጀ የአስከሬን ምርመራ በአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን 85 ጉድጓዶች፣ በመስጊድ 2፣ በእርሻ ቦታዎች 24 እና 6 የጅምላ መቃብር ጉድጓዶች ተከፍተው ምርመራ መካሄዱ ተነግሯል።

በቀጣይም ይህ የጥፋት ሃይል አገር ለማፍረስ የሄደበትን ርቀት ለታሪክ ሰንዶ ለማስቀመጥና የዘረፉቸውን ንብረቶች ለማስመለስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም