በደል ያደረስንበት የመከላከያ ሠራዊት እየተንከባከበን ነው... የተሃድሶ ሰልጣኞች

67

ጥር 21/2013 (ኢዜአ) ከህወሃት የጥፋት ሃይል ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩና አሁን በተሃድሶ ስልጠና ላይ የሚገኙ ታጣቂዎች "ውስጥ ውስጡን ተዘጋጁ ተባልን እንጂ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እንደምንዋጋ አናውቅም ነበር" ይላሉ።

አዋሽ አርባ በሚገኘው የደቡብ ዕዝ የስልጠና ማዕከል በልዩ ሃይል፣ በሚሊሻና በተለያየ መልኩ ከጁንታው ጎን ተሰልፈው ውጊያ ላይ የቆዩ ከ700 በላይ ታጣቂዎች በተሃድሶ ስልጠና ላይ ይገኛሉ።

የተሃድሶ ሰልጣኞቹ የዕድሜ ክልል ከታዳጊ ልጆች እስከ አዛውንት ነው።

የመከላከያ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ወደ ስፍራው ተጉዘው ሰልጣኞቹ የሚገኙበትን ሁኔታ አይተዋል።

ሰልጣኞቹ ጁንታው ውስጥ ለውስጥ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲነገራቸውና ሲያስታጥቃቸው መቆየቱን ይናገራሉ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት ሲፈፀም እነሱም ተገደው ከጁንታው ጎን መሰለፋቸውን ተናግረዋል።

በመከላከያ ሰራዊት እጅ ከገቡ በኋላ ጥሩ አያያዝ እየተደረገላቸው እንደሆነም ገልፀዋል።

እኛ በደል ያደረስንበት የመከላከያ ሰራዊት ከማንም በላይ እየተንከባከበን ይገኛል ሲሉም ምስጋና አቅርበዋል።

እየተሰጣቸው ባለው የተሃድሶ ስልጠና በአጠቃላይ አገራዊ ጉዳይ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እያገኙ መሆኑንም ተናግረዋል።

የስልጠናና የተሃድሶ ማዕከሉ አስተባባሪ ኮሎኔል ብርሃኑ አሰፋ በስልጠና ላይ የሚገኙት ግለሰቦች መሳሪያ ታጥቀው ከጥፋት ቡድኑ ጎን ተሰልፈው የነበሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የመከላከያ ኅብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀስን ኢብራሂም ግለሰቦቹ ሕገ መንግስቱን አደጋ ላይ ለመጣል ጭምር የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል።

አብዛኞቹ ያለፍላጎታቸው የገቡ ቢሆኑም ጁንታው በከፈተው አገር የመናድ ጦርነት የተሳተፉ በመሆኑ ትምህርትና ስልጠና ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ የጁንታውን ውሸት መረዳት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ትምህርትና ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው አገርና ሕዝባቸውን መካስ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ የጥፋት ድርጊት ለተሳተፉ ግለሰቦች የተሃድሶ ስልጠና የመስጠቱ ተግባር እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም