በክልሉ የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግርን ለመፍታት መንግስት በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግርን ለመፍታት መንግስት በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ

አሶሳ፤ ጥር 20/ 2013(ኢዜአ) ፡-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት መንግስት ህዝቡን በማደመጥ በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከንግድ ባንክ ጋር በመተባበር በሠላም፣ አብሮነት፣ ግጭት አፈታትና የሃይማኖት ብዝሃነት አያያዝ ዙሪያ ለሀይማኖት መሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወርቁ ሊበን እንዳሉት ክልሉ የበርካታ ብሄረሶቦች መኖሪያ ነው፡፡
የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያውያን እንደ ሃገር ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር ለክልሉ ህዝቦች የቅርብ ተስፋ ይዞ እንደመጣ ጠቅሰው ተስፋው በጸጥታ ችግር እንዳይደናቅፍ የክልሉ መንግስት በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል፡፡
በክልሉ ግለሰቦችም ሆኑ ማህበረሰብ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት ጆሮ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በብሔሮች መካከል እኩልነት ማስፈን ይገባል ያሉት ተሳታፊው የክልሉ መንግስት ይህን መሠረት አድርጎ ቢሠራ የመተከል ሠላም ይመለሳል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ባህላዊ እና ሃማኖታዊ እሴቶች ለክልሉ ሠላም ግንባታ ማዋል አለብን ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሃይማኖት ታደሰ ናቸው፡፡
ለዚህ ደግሞ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸውን ክብር በተግባር ማሳያት እንዳለባቸው አመልክተው ለዚህም የሃይማኖት አባቶችም መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
መላከ ጸሐይ ቆሞስ አባዘካሪስ ጸጋው በበኩላቸው በክልሉ ግጭት ሲከሰት የሚመለከታው የመንግስት አካላት ችግሮችን በእንጭጩ መቅጨት ሲገባቸው በዝምታ ማለፋቸው ግጭትን አባብሷል ብለዋል፡፡
አሁንም ችግሩን በግልጽ ተነጋግሮ ለመፍትሔው መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ የክልሉ ሠላም እንዲመለስ በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ የመተከል ግጭት የሁላችንንም አንገት ያስደፋ ዘግናኝ ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፌደራል እና ክልል መንግስታት በቅንጅት ኮማድ ፖስት አደራጅተው የማያዳግም እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው መሰል የውይይት መድረኮችን በማስቀጠል ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለበት ክልል ነው፡፡
የኢትዮጵያ እናቶች አሻራቸውን ለማኖር እንጨት ለቅመው በቆጠቡት ሃብት ጭምር በክልሉ እየተገነባ ያለውን የህዳሴ ግድብን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አደራ የሆነው የህዳሴው ግድብ በክልሉ ህዝብ እጅ ይገኛል፤ ክልሉን በማተራመስ የግድቡን ግንባታ ማስቆም የግጭቱ ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ልትረዱ ይገባል ብለዋል፡፡
በአሶሳ ከተማ ከትናንት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ዛሬ እኩለ ቀን መጠናቀቁን ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል፡፡