የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደህንነት ተቋማት በአካባቢያዊ ጉዳዮች እና በአቅም ግንባታ መስኮች በትብብር ለመስራት ተስማሙ

127

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደህንነት ተቋማት በአካባቢያዊ ጉዳዮች እና በአቅም ግንባታ መስኮች በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ተገለጸ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከደቡብ ሱዳን የውስጥ መረጃ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል አኮል ኮር ኩክ ጋር ዛሬ በሁለትዮሽ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደህንነት ተቋማት በአካባቢያዊ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የነበራቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

በተለይ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን፣ ሽብርተኝነትንና በድንበር አካባቢ የሚታዩ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ቀጣናዊ ሰላምንና ደህንነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደህንነት ተቋማት በአቅም ግንባታ መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አማካኝነት ለደቡብ ሱዳን ባለሙያዎች ስልጠናዎች ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም