የኢትዮጵያና ሱዳንን የድንበር ጉዳይ መፍታት የሚቻለው አገራቱ ባቋቋሟቸው መዋቅሮች ብቻ መሆኑ ተገለጸ

90

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያና ሱዳንን የድንበር ጉዳይ መፍታት የሚቻለው ሁለቱ አገሮች ባቋቋሟቸው መዋቅሮች ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አቶ ውሂብ ሙሉነህ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የድንበር ጉዳዩ በመነጋገርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገች መሆኑንም ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አቶ ውሂብ ሙሉነህ ለኢዜአ እንደገለጹት የሁለቱ አገሮች የድንበር ማካለል ጉዳይ ለ118 ዓመታት የዘለቀ ነው።

እ.አ.አ በ1902 ጉዊን የተባለ እንግሊዛዊ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የማካለል ስራ መስራቱንና የማካለሉን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርት ማቅረቡን አስታውሰዋል።

ይሁንና ጉዊን የድንበር ማካለሉን ያደረገው ያለ ኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ሪፖርቱን ውድቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ አገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት እ.አ.አ በ1972 የሀሳብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመው ድንበራቸውን እንደገና ለማካለል መስማማታቸውን ነው አቶ ውሂብ ያስረዱት።

በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ አገራት የሚቀበሉት የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የድንበር ነባራዊ ሁኔታው ባለበት ተከብሮ እንዲቆይ መስማማታቸውን አመልክተዋል።

እ.አ.አ በ2002 ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣ የጋራ ድንበር ቴክኒክ ኮሚቴ እና የጋራ ልዩ ኮሚቴ አቋቁመው ለድንበሩ ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

የድንበር ኮሚሽኑ በኮሚቴዎቹ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን በመገምገም ለአገራቱ መንግስታት ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የጋራ የድንበር ቴክኒክ ኮሚቴው በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ቅኝት ማድረጉም ይታወሳል።

የጋራ ልዩ ኮሚቴው በሀሳብ ልውውጥ ስምምነቱ አማካኝነት የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እንዲደርሱ የሚያስችሉ ስብሰባዎችን አድርጎ የመጨረሻ ሪፖርት ባላቀረበበት ሁኔታ ሱዳን ሃይል ተጠቅማ የኢትዮጵያ መሬት መያዟን ነው አቶ ውሂብ የገለጹት።

ሱዳን ይህንን ማድረጓ እ.አ.አ በ1972 የሀሳብ ልውውጥ መሰረት አማካኝነት ነባራዊ ሁኔታውን የማስቀጠል ስምምነት መጣሷንና ለፈረመችው ስምምነት ተገዢ አለመሆኗን ተናግረዋል።

ሱዳን ያስመለስኩት መሬቴን ነው በሚል የምታቀርበው ሀሳብም ስምምነቱን ያላከበረ እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳያቸውን ለመፍታት ያቋቋሟቸውን የጋራ መዋቅሮች ተጠቅመው መፍትሔ ማበጀት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የድንበር ጉዳዩ በመነጋገርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አስፈላጊውን ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የድንበር ጉዳዮች እልባት ያገኙት በውይይት እንደሆነና ሱዳንም ይሄን ተገንዝባ ጉዳዩን በንግግር ለመፍታት ራሷን ማዘጋጀት እንደሚገባት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ጉዳዩን በሚመለከት በታህሳስ 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም በካርቱም የተወያዩ ሲሆን፤ቀጣይ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም