የምርት ጥራትና ደረጃን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በትብብር መሥራት ይገባል- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

125

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የምርት ገበያ ባለሥልጣን የምርት ጥራትና ደረጃን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ይበልጥ ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡ 

በምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንን የስድስት ወራት አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል፡፡

በመድረኩም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሁለቱ ተቋማት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሥራዎችን በቅንጅት በመሥራት በኩል ክፍተት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በታቀደና በተደራጀ አኳኋን በመሥራት፣ በቅንጅታዊ አሰራር እንዲሁም በደንበኛ አያያዝ በኩል ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተገልጿል።

በተለይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተለያዩ ሥፍራዎች ባሉት መጋዘኖች የጆንያ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ መኪኖች ለረጅም ጊዜ ያለጭነት መቆማቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።

በድሬዳዋ፣ በዲላና በሃዋሳ ላሉ የጉልበት ሠራተኞች የደህንነትና የንፅህና መጠበቅያ ቁሳቁስ በማሟላት ረገድም ክፍተት መኖሩ ተነስቷል፡፡

ለገበያ የሚቀርብ ምርት ደረጀውን እንዲጠብቁና በዓለም ገበያ የኢትዮጵያ ምርት ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በበኩላቸው ከደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ያም ሆኖ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሄደው የሕግ ማስከበር ሥራና በሌሎች ምክንያቶች በቡናና በሰሊጥ ምርት አቅርቦት ላይ ዘንድሮ ቅናሽ መታየቱንም ጠቁመዋል።

ምርቶች ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓት እንዲገቡ በየጊዜው ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ ድጋፎችን በማድረግ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 6 ወራት 345ሺህ 398 ሜትሪክ ቶን ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ 319ሺህ 629 ሜትሪክ ቶን በመሰብሰብ የዕቅዱን 93 በመቶ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በግማሽ ዓመቱ 323 ሺህ 694 ሜትሪክ ቶን ምርት ለመሸጥ በታቀደው መሰረት 320ሺህ 140 ሜትሪክ ቶን ለገበያ በማቅረብ 99 በመቶ አፈፃፀም መመዝገቡንም ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኡሌሮ ኦፒዮው በበኩላቸው ከተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት ጋር ሥራዎችን በቅንጅት በመሥራት በቀጣይ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም