የጅምላ ዘር ጭፍጨፋ ሰለባ ቀን ሲከበር በገሐዱ ዓለም የሚታዩ ማንነት ተኮር ጥቃቶችን በመከላከል ሊሆን ይገባል - ተመድ

76

ጥር 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) የጅምላ ዘር ጭፍጨፋ ሰለባ ቀን ሲከበር ዛሬም በገሐዱ ዓለም የሚስተዋሉ ማንነት ተኮር ጥቃቶችን በመከላከል ሊሆን እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ ጥሪ አቀረቡ።

የዓለም 'የጅምላ ዘር ጭፍጨፋ ሰለባዎች ቀን' በአዲስ አበባ ተከብሯል።

ዕለቱ ከዛሬ 76 ዓመታት በፊት በአዶልፍ ሒትለር መራሹ የጀርመን የበላይነት አቀንቃኝ 'ናዚ' ቡድን በአይሁዳዊያን ላይ የፈፀመውን ጅምላ ጭፍጨፋ መሰረት በማድረግ በመንግስታቱ ድርጅት ታውጆ በየዓመቱ ይከበራል።

እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ በየዓመቱ ጥር 19 በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ የሚገኘው የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባዎች ቀን ዛሬም በኢትዮጵያ የእስራኤልና የጀርመን ኤምባሲዎች አዘጋጅነት ተከብሯል።

የተመድ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ በመታሰቢያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት "በናዚና ግብረ አበሮቹ 6 ሚሊዮን አይሁዳዊያንና ሌሎችም በጅምላ የግፍ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑበት ዕለት ሲዘከር ዛሬም በማኅበረሰባችን ውስጥ ያላባራውና ዳግም እያንሰራራ ያለው ጭፍን ጥላቻ እያሳሰበን ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

"በጀርመን ናዚ ጅምላ ጭፍጨፋ ሁለተኛው ሚሊኒየም በአይሁዳዊያን ላይ የተፈጸመ የመድሎ፣ የጥቃት፣ የጥላቻና የጅምላ ግድያ ማብቂያ ሁነት መሆን ነበረበት" ብለዋል።

ዳሩ ግን የፀረ ፅዮናዊነት እንቅስቃሴ ዛሬም ሕያው ሆኖ የሚታይ ያልቆመ አመለካከት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በዓለም ላይ የዘር የበላይነት አቀንቃኞችና የናዚ አስተሳስብ ደጋፊዎች በድንበር ዘለልነት እያንሰራሩ፣ እየተደራጁ የናዚን ጭፍጨፋ ጨምሮ የጭፍጨፋ ታሪክ የመካድና የማዛባት አባዜ እንደተጠናወታቸው አብራርተዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት አናሳ ወገኖች፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ብሄር፣ አካል ጉዳትና ስደተኝነት ላይ ያተኮሩ የማንነት ጥቃትና መድሎዎች እየደረሱ ስለመሆኑ ገልጸው፤ "በትብብርና በፍጥነት ማስቆም ይገባል" ብለዋል።

የጅምላ ዘር ጭፍጨፋ ሰለባ ቀን ሲከበር ዛሬም በገሐዱ ዓለም የሚስተዋሉ ማንነት ተኮር ጥቃቶችን ለመከላከል "በሰውነታችን ተሳስረን በጋራ ለመስራት በመወሰን ሊሆን ይገባል" ነው ያሉት።

የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባዎችን ስንዘክርም እኩልነት፣ ፍትህና የሁሉም ሰዎች ክብር የተጠበቀባት ዓለም እንድትሆን የራሳችንን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም