በካሳ ክፍያ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረው የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራ ተጀመረ

120

ደሴ፣ ጥር 19/2013 (ኢዜአ) ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተስተጓጉሎ የነበረው የአዋሽ - ኮምቦልቻ - ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ችግሩ ተፈቶ ስራው የቀጠለ መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ ገለጹ።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነውና በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ችግር በመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ ያለአገልግሎት የቆየውን የአዋሽ - ኮምቦልቻ የባቡር መስመር በቅርቡ ስራ ለማስጀመር እየተሰራ እንደሆነም ተነግሯል ።

ስራ አስኪያጁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሁለት ምዕራፍ እየተሰራ የሚገኘው የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ 390 ኪሎ ሜትር የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ በ2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነበር።

የሁለተኛው ምዕራፍ ከኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት ስራው ተስተጓጉሎ መቆየቱን አመልክተዋል።

"በአጠቃላይ ከኤሌክትሪክ አቅርቦትና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በሁለቱም ምዕራፎች የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራው ለስምንት ወር ተስተጓጉሎ ቆይቷል" ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ለ480 አርሶ አደሮች 100 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ የካሳ ክፍያ በቅርቡ በመከፈሉ በሁለተኛው ምዕራፍ ተስተጓጉሎ የነበረው የ50 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታ ካለፈው ወር ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ አጠቃላይ ስራ 82 በመቶ መጠናቀቁን የጠቆሙት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ፤ ቀሪውን ስራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታው 99 በመቶ ተጠናቆ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ወደ ሙከራ ሳይገባ የቆየውን አዋሽ - ኮምቦልቻ የባቡር መስመርን ስራ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ በጊዜ መራዘም ምክንያት ተጨማሪ ወጪ እንዳይጠይቅ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአዋሽ - ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት የ51 ድልድዮችና የ12 ዋሻዎች ግንባታ ያካተተ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

አዋሽ - ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የምድር ባቡር ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም