ቤተ ክርስትያኗ የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የምሥጋና ሥነሥርዓት አካሄደች

ጋምቤላ ፤ ጥር 19/2013(ኢዜአ) ቤተ ክርስቲያኗ በጋምቤላ ከተማ ለአምስት ቀናት የተከበረው የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የጸጥታ አካላት የምሥጋና ሥነ-ሥርዓት አካሄደች።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲቲያን የጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቄለምና ምዕረብ ወለጋ አህጉረ ስብክት ሊቀ ጳጳስ ብፁ አቡነ ሩፋኤል እንዳሉት ጥምቀት በጋምቤላ ከተማ ከሌሎች አካባቢዎች በተለዩ መልኩ ለአምስት ቀናት ሲከበር ቆይቷል።

በተመሳሳይ ዘንድሮም የተከበረው የጥምቀት በዓል ያለምን የፀጥታ ችግር በሠላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌደራልና የክልል ፖሊስ አባላት ቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ምሥጋና ታቀርባለች ብለዋል።

እንደ ሀገር ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት በተወሰኑ አካባቢዎች የጥምቀት በዓል ያልተከበረባቸው ቦታዎች መኖራቸውን አውስተዋል።

ይሁን እንጂ በጋምቤላ ከተማና ሌሎች የክልሉ አካባቢው ባለው ሠላም፣ የህዝቦች አንደነትና የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት በዓሉ ለሌሎች አካባቢዎች ተምሳሌት በሚሆን መልኩ ያለምንም ችግር በሠላም መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ይህንም ታሳቢ በማድረግም ቤተ ክርስቲያኗ ለጸጥታ አካላት የምሥጋናና እራት ግብዣ ሥነ-ሥርዓት ማዘጋጀቷን ገልጸው በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የጸጥታ አካላትና ለመላው የክልሉ ህዝብ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ ብለዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ከተሳተፉ የፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል ዋና ኢንስፔክተር ዳንታሞ ማሎሮ በሰጡት አስተያየት የፌደራልና ክልል ፖሊስ አባላት በጋር በመሆን ባካሄዱት የተቀናጀ ሥራ በዓሉ በሠላም ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።

’’ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ ምስጋና መሰጠት ለነገ የሞራል ስንቅ እንደመስጠት ነው’’ እንዳሉት ሁሉ ቤተ ክርስቲያኗ ያደረገችው የምሥጋና የእራት ግብዣ ለቀጣይ ሥራቸው ብርታት እንደሚሆናቸው በመግለጽ አመስግነዋል።

የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በነበረው ቅንጅታዊ አሰራር በዓሉ ያለ ምንም እንከን በሠላም መጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ አባል ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ በደቀ ናቸው።

ቤተ ክርሲቲያኑ በዓሉ በሠላም መጠናቀቁን በማስመልከት ለጸጥታ አካላት ላዘጋጀችው ሥነ-ሥርዓት ምስጋና አቅርበዋል።

ኮንስታብል ሄኖክ በምታፍ በበኩላቸው በዓሉ ያለምንም ችግር በሠላም መጠናቀቁን በማስመልከት ቤተ ክርሰቲያኗ ለጸጥታ አካላት ያዘጋጀችው የምሥጋና ሥነ-ሥርዓት ብርታት እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም