ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለጸ

248

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2013 ( ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

የጽህፈት ቤቱ የሚዲያ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር  አቶ ሀይሉ አብርሃም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለግድቡ ግንባታ እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም ለግድቡ ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ድጋፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሊት መከናወኑ ደግሞ ህብረተሰቡ ለግድቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ እንዲጨምር መነሳሳት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ድጋፍም ኢትዮጵያውያን ለሀገር ልማትና ሉዓላዊነት ያላቸውን አቋም በግልጽ የሚያሳይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የሲቪክ ማህበራት፤፣ አርቲስቶች፣ድምፃዊያን፣ ኮሜዲያኖችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለግድቡ ግንባታ በሚደረገው ገቢ ማሰባሰብ ስራ ላይ በሙያቸው አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ህብረተሰቡ እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ ግንባታ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።