ለኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ የሰለጠነ የሰው ሀይል አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ... አቶ ንጉሱ ጥላሁን

136

ደብረብርሃን፤ ጥር 19/2013(ኢዜአ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ የሰለጠነ የሰው ሀይል አቅርቦት እንዲኖር በየደረጃው ያለው አመራር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የፌደራል የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

የኮሚሽኑ ሰራተኞች የደብረ ብርሀን ኢንዱስትሪ ፓርክን  በጎበኙበት ወቅት አቶ ንጉሱ እንዳሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ለሃገሪቱ  አማራጭ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኛ ናቸው።

የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና ክህሎት  ሽግግር የሚደረግባቸው መሆኑንም ጠቅሰው፤ የተሻለ የስራ እድል በመፍጠርም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይህን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በደብረ ብርሀን ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ በገቡ ባለሀብቶች የሚቀጠሩ ወጣቶች ስራ ጥለው የመሄድ ችግር እንዳለ መረዳታቸውን አመልክተዋል።

በቅርብ ስራ በጀመረው የስፔንናዊ ባለሀብት ንብረት የሆነው ኬኬ ማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ  200 የሚደርሱ ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው መልቀቃቸውንም ጠቁመዋል።  

የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ከፍ ብሎ እያለ በኢንዱስትሪው ተመልምለው የሚቀጠሩ ሰራተኞች ስራቸውን መልቀቅ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ ለዚህም የአካባቢው አመራር በቂ የሰለጠነ የሰው ሀይል አቅርቦት እንዲኖር ምልመላና መረጣ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑም በኢንዱትስሪ ፓርኮች የሚሰማሩ ሠራተኞች በአግባቡ የሰለጠኑና  በቂ እውቀት ያላቸው ሆነው እንዲቀርቡ በትብብር ይሰራል ነው ያሉት።

የደብረ ብርሀን ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋይናስና አስተዳደር ክፍል ሀላፊ አቶ አባይነህ ደመቀ በበኩላቸው ከተገነቡት ስምንት ሼዶች መካከል አምስቱ ለባለሀብቶች መተላለፋቸውን አስረድተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ባሳደረው ጫና ሶስቱ ባለሀብቶች ማሽነሪ ቢያቀርቡም ወደ ስራ እንዳልገቡ ጠቁመው፤ በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችላቸውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኬኬ ማኑፋክቸሪንግ  ኢንዱስትሪ ማሽኖችን በሁለት ሼዶች ውስጥ በመትከል  የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል ያመረተውን ሹራብ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ከኢንዱስትሪ ፓርኩ መሬት ተረክቦ ግንባታ ላይ የነበረው የ“ፖርቱማንት ብቅል ፋብሪካ“ በቅርቡ ስራ በመጀመር በአጭር ግዜ ውስጥ ያመረተውን 100 ቶን የብቅል ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ መሆኑን  ተናግረዋል።

በባለሀብቶች የሚነሱ የስልክ፣ የኢንተርኔትና  መንገድ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኬኬ ማኑፋክቸሪንግ ማኔጀር አቶ ሰለሞን ደመወዝ እንዳሉት 240 የማምረቻ ማሽኖችን ለመትከል ቢታሰብም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እስካሁን ተተክለው ማምረት የጀመሩት 132 ማሽኖች ናቸው።

በቅርቡ ቀሪ ማሽኖችን በመትከል በሙሉ አቅሙ ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አመልክተው፤ ስራ በጀመሩ የተመረተ ሹራብ ቀጥታ ለውጭ ገበያ በመላክ ሁለት ሚሊዮን 300ሺህ  ዶላር ሽያጭ መከናወኑን ተናግረዋል።

ለ727 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩንና ከነዚህም  96 ከመቶ  ሴቶች እንደሆኑ አስታውቀዋል።

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወይዘሪት ፌቨን መለሰ በሰጠችው አስተያየት እስካሁን በአሰሪና ሰራተኞች መካከል መልካም ግንኙነት እንዳለ ገልፃለች።

በድርጅቱ ሲቀጠሩም  በቂ ሥልጠና ተሰጥቷቸው መሰማራታቸውን ጠቅሰው፤በወር የሚከፈላት አንድ ሺህ 200 ብር ደመወዝ በቂ ባለመሆኑ መስተካከል እንደሚገባው አስተያየት ሰጥታለች።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም