አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ለአውሮፓ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮችና የልማት ቋሚ ኮሚቴዎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚለከት ገለጻ አደረጉ

647

ጥር 19/2013 (ኢዜአ) በቤልጂዬም፣ ሉክሰምበርግ እና በአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ለአውሮፓ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮችና የልማት ቋሚ ኮሚቴዎች በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ገለጻ አደረጉ።

በገለጻቸው መንግስት በትግራይ ክልል አስፈላጊውን የሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

አምባሳደሯ ከኮሚቴዎቹ አባላት ጋር በነበራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል እየተደረገ ስላለው ሰባዊ ድጋፍ፤ ክልሉን መልሶ የማቋቋም ስራዎችና የሕዝብ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት በክልሉ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ፣የተፈጸሙ ወንጀሎችን መመርመር፣ሕዝብን የማረጋጋትና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ስድስተኛው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫና የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ጉዳይ በሚለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ፓርላማ የልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶማስ ቶቤ በበኩላቸው በትግራይ ክልል የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር በመሆን ከ15 ወራት በፊት ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፤  በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያ የቀጠናው አንጸባራቂ የስኬት ተምሳሌት እንደምትሆን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአውሮፓ ሕብረት የአውሮፓ የውጪ ጉዳዮች አገልግሎት፣ዓለም አቀፍ የትብብር ኮሚሽን እና የሕብረቱ የቀውስ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽን በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።

የአውሮፓ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች የልማት ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር የተደረገው የሀሳብ ልውውጥ የአውሮፓ አገራት በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ሚዛናዊ አተያይ እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም በብራስልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።