በደሴ ከተማ ጤና ተቋማት የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ሊስተካከል ይገባል…ቋሚ ኮሚቴው

561

ደሴ፤ ጥር 19/2013(ኢዜአ) በደሴ ከተማ በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተትና የግንባታ መጓተት ሊስተካከል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ህጻናት፤ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሉኡካን  አባላት በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያዎች የአገልግሎት አሰጣጥና ግንባታ እንቅስቀሴን ተመልክተዋል፡፡

የሉኡካኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ሙንተሃ ኢብራሂም በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት በተመለከቱበት ወቅት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፤ የመረጃ አያያዝ ክፍተት፤ የማስፋፊያ ግንባታዎች መጓተት፤ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎት ጥበትና የግብዓት አቅርቦት  ክፍተቶች መኖራቸውን  አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

አብዛኞች የጤና ተቋማትም ጤና ሚኒስቴር ካስቀመጠው መስፈረት  በታች አገልግሎት ሲሰጡ ማስተዋላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውንና የተሻለ አገልግሎት እንዳያገኝ ስለሚያደርጉ በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከተቋማቱና ክልሉ አቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ   በፌደራል መንግስት በኩል  መስተካከል እንዲችሉ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው  አባል ወይዘሮ ሪሃና መሃመድ በበኩላቸው በጥቃቀን ችግሮች ምክንያት  ህብረተሰቡ መጉላላት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

በሆስፒታሎችም ሆነ ጤና ጣቢያዎች የሚገጥመውን ችግር በቅንጅት በመፍታት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ቋሚ ኮሚቴውም ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

 ከከሚሴ ከተማ መጥተው ለአገልገሎት በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነበሩት አቶ ሐሰን ተማም እንደተናገሩት በሆስፒታሉ ከፍተኛ መጨናነቅና የታማሚ ብዛት በመኖሩ አገልግሎት አሰጣጡ ቀርፋፋ ነው፡፡

ካርድ ለማውጣት ብቻ ከአንድ ቀን በላይ እንደሚወስድ ጠቁመው፤ በአልጋ ጥበት መሬት ላይ የሚተኙትና መድሃኒት የለም እየተባሉ እንደሚቸገሩም ገልጸዋል፡፡

እሳቸውም አጎታቸው በድንገት ታመው ለከፍተኛ ህክምና ተብለው  ቢመጡም እየተጉላሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የደሴ ከተማ  አስተዳደር ጤና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልሃሚድ ይመር እንዳሉት ችግሮች ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ በመሆናቸው በቀላሉ ማስተካከል አልተቻለም፡፡

”የህክምና ቁሳቁስና የባለሙያ እጥረት እንዲሁም  የመድሃኒት አቅርቦት ችግር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቁመው፤ ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የሚችሉትን ፈጥነው ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማው ካሉ ስምንት ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ሦስቱ ብቻ የተሻሉ እንደሆኑ የጠቀሱት  ኃላፊው ችግሩን ለማቃለል  በክልልና ፌደራል መንግስት የሚሰሩ የግንባታ ማስፋፊያዎች ለረጅም ጊዜ እየተጓተቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀጣይም ቀናትም የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ ሌሎችንም ተቋማት እንደሚመለከቱ ይጠበቃል፡፡