በአምቦ ወረዳ ለ66 አካል ጉዳተኞች የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

61

አምቦ፤ ጥር 19 /2013 (ኢዜአ) በአምቦ ወረዳ ለ66 አካል ጉዳተኞች ከ205 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፍ የተደረገው አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በወረዳው በተከበረበት ወቅት ነው፡፡

የወረዳው ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት  ሃላፊ አቶ አያንሳ ዱጉማ በወቅቱ  እንዳሉት ድጋፍ የተደረገው  በአካባቢው ለችግር ለተጋለጡ አካል ጉዳተኞች  ጫማና ብርድ ልብስ ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ነው።

ለድጋፉ ከ205 ሺህ ብር በላይ ወጪ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም እገዛ ላደረገላቸው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ፣ ባለሀብቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡


አካል ጉዳተኞች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በመጠበቅ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ እንዲቻል የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም አመልከተዋል፡፡


የአምቦ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኩመላ ሂርጳ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች የአእምሮ ህመምተኞች ስላልሆኑ ትኩረት ቢሰጣቸው ሁሉንም ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡


አካል ጉዳተኞች ከጤነኞች እኩል  በሁሉም የሥራ መስክ ቢሳተፉ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሀገሪቱም አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡


አካል ጉዳተኞችም የጠባቂነት  አመለካከትን በመተው በልማትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በማሳተፍ ያላቸውን አቅም መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡


ድጋፍ ከተሰጣቸው መካከል አቶ ፍቃዱ አራርሳ በሰጡት አስተያየት በእግራቸው ህመም ምክንያት እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መስራት ስለማይችሉ ለችግር መጋለጣቸውን  ጠቅሰው፣ አሁን ለተደረገላቸው የአልባሳት እገዛ አመስግነዋል፡፡


መንግስት ችግራቸውን አይቶ ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ ቢያመቻችላቸው ሰርተው ራሳቸውን መለወጥ እንደሚችሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


ወይዘሮ ሙሉ ፉርጋሳ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው መንግስት በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


በአምቦ ወረዳ 2ሺህ400 የአካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ከወረዳው ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት  የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም