በሀዋሳ ዙሪያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የእረቀ ሰላም ኮንፍረንስ ተካሄደ

60

ሐዋሳ ጥር 19/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ሲራሮ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የሚያስችል የህዝብ ለህዝብ ግንኙንትና የእረቀ ሰላም ኮንፍረንስ ተካሄደ።

በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሻማና ከተማ የህዝብ ለህዝብ የእርቅ ሥነ-ስርዓቱን በምርቃት  ያስጀመሩት  የኦሮሚያና የሲዳማ አባገዳዎች፣ የሀገር  ሽማግሌዎችና  የኃይማኖት  አባቶች ናቸው።

አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች በወቅቱ እንደገለፁት  በሁለቱ  ወንድም ህዝቦች መካከል በተፈጠረው ሁከት በህዝቦች መካከል ከፍተኛ ቅሬታ በመፈጠሩ እጅግ አሳዝኗቸዋል።

"ቅሬታውን ለመፍታት በሻማና  የተዘጋጀው የእርቀ ሰላም መድረክ የሁለቱን ህዝቦች ፍቅር መልሶ ከማጠናከር ባለፈ ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን አብሮ የመኖር ወርቃማ እሴቶቻችንን በተግባር ያየንበት ስለሆነ ተደስተናል" ብለዋል።

ከሁለቱም ወገን በግጭቱ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችና የአካባቢው ነዋሪዎች በአባገዳዎች፣  በሀገር ሽማግሌዎችና በኃይማኖት አባቶች ፊት  ቀርበው በመሳሳምና  ይቅር  በመባባል  እርቀ ሠላሙን አከናውነዋል።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ  ጢሞቲዎስ  "በመንግሥት  በሚተዳደረው ቢሊቱ እርሻ ልማት ላይ ያለአግባብ የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶ ባለፉት ስድስት ዓመታት የአካባቢው ሰላም በመታወኩ ምክንያት በቁሳዊና ሰብዓዊ ሀብታችን ላይ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል።

"የሁለቱም ማህበረሰብ ክፍሎች የእርሻ ተረፈ ምርትና በቅጥር ሰራተኝነት ሲጠቀሙ ነበር" ያሉት ኃላፊው በተፈጠረው ግጭት እርሻው ለዓመታት ሳይታረስ  መቆየቱን አስታውሰዋል።

የእርሻው ጉዳይ በሁለቱ ክልል መንግስታት በውይይት ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ 3 ሺህ 700 ሄክታር የእርሻው ይዞታ በሰብል እንዲለማ በማድረግ ግጭቱንም በእርቅ መቋጨት መቻሉን አስታውቀዋል።

በቀጣይ የሁለቱንም ክልል ህዝቦች በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች የሚያስተሳስሩ የልማት ፕሮጀክቶች በማካሄድ የአካባቢውን ፀጥታ ወደ ነበረበት አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተወካይና የምእራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ያልተዋጠላቸው አካላት በጠነሰሱት ሴራ በክልሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ችግር መፈጠሩን አስታውሰዋል

የተፈጠረውን ችግር  ከመሰረቱ ለመፍታትና እረቀ ሰላም በማውረድ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አብሮነትና ፍቅር እንዲጎለብት በተደረገው ጥረት ውጤት መገኙን ገልፀዋል።

ከዚህ በኋላ ህዝቡ ካለፈው ችግር  በመማር የአካባቢውን ሰላም በመንከባከብ ድህነትን ለማሸነፍ ፊቱን ወደ ልማትና እንድነት እንዲያዞር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘውን ሠላም እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል።

በእረቀ ሰላምና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለተሳተፉ አባገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሸማግሌዋች ምስጋና አቅርበዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የሲራሮ ወረዳ ነዋሪ አቶ ባባሶ ጢቃሞና የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አቶ ግርማ ሪቂዋ "በብሄርና ጎጥ እየተከፋፈሉ መጠፋፍት የፈጣሪን ቃል ያለመጠበቅ ከፍተኛ ችግር በመሆኑ ሁሉም ከዚህ እኩይ ተግባር ፈጥኖ መላቀቅ አለበት" ብለዋል።

"በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው ግጭት በልማታችንና ሰላማችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮብን አልፏል" ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ችግሩ እንዳይደገም ለሠላም ዘብ በመቆም  ሁሉም በጋራ መስራት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

በዕለቱ ለእርቀ ሰላሙ ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላት የእውቅና ሠርተፊኬትና የባህል አልባሳት ተበርክቶላቸዋል።

እርቀ ሰላም ኮንፍረንሱ በኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች ትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም