የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያዩ

298

ጥር 18/2013(ኢዜአ) የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያዩ።

በአዲስ አበባ ከሚገኙት የአውሮፓ ህብረት የትብብር ዘርፍ ኃላፊ ሚስተር ኤሪክሀበር ጋር በትግራይ እየተካሄደ ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች በተመለከተ ሚኒስተሩ ውይይት አድርገዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ ድጋፍን አስመልክቶ  ስጋት ሊኖረው እንደማይገባና በትግራይ ያለው የፀጥታ ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉን አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም በብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስተባባሪነት ከአገር ውስጥና ከውጪ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እና የመድኃኒት አቅርቦቶች ለአብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢዎች ተደራሽ እየተደረጉ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለሴቶች፣ ለህፃናት፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በማጠናከር ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውንም ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።