ቋራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቀሶችን በድጋፍ አገኘ

558

መተማ ጥር 18/2013(ኢዜአ ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ለሚገኘው የቋራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከአንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶችን በድጋፍ አገኘ።

የህክምና ቁሳቁሶቹን  ድጋፍ ያደረጉት ”የኢትዮ -እስራኤላዊያን ወገን ለወገን ደራሽ የድጋፍ ማህበር” አባላት ናቸው።

የማህበሩ ተወካይ አቶ ደሴ አምሳሉ ቁሳቁሱን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ከዚህ በፊት ከሆስፒታሉ ሠራተኞች እና ተጠቃሚዎች ጋር በመመካከር ችግሮችን የመለየት ስራ ተከናውኗል።

ሆስፒታሉ ያለበትን እጥረት በመለየትና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን የህክምና ቁሳቁሶች ከአንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው  ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የህክምና ግብዓቶቹ በተለይም የእናቶችን ህክምና አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚግዙ ገልጸዋል።

ከድጋፉ  መካከል የላቦራቶሪ ማሽን፣ አልትራ ሳውንድ፣ ማቀዝቀዣ  ማሽንና ሌሎችም የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የህክምና ቁሳቁሶቹ ሆስፒታሉ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ፣  በግብዓቶች እጥረት ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ የሚላኩ  ተገልጋዮችን እንግልትና ወጪ ለመቀነስ እንደሚረዳ  የተናገሩት ደግሞ በሆስፒታሉ የእናቶችና ህፃናት ህክምና አስተባባሪ አቶ መኮንን ባዩ ናቸው።

የቋራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤፍሬም ወርቁ በበኩላቸው  ሆስፒታሉ አዲስ በመሆኑ አሁን የተደረገለት የግብዓት ድጋፍ አቅሙን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸው ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ሌሎች አስፈላጊ የህክምና ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ ተናገረዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት የወረዳው አመራሮችና ሆስፒታሉ ሠራተኞች ተገኝተዋል።