ቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ዩኒየን ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ገበያን እያረጋጋ ነው

71

ፍቼ ጥር 18/2013(ኢዜአ) በፍቼ ከተማ የሚገኘው ቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን እህል ጨምሮ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለአካባቢው ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን እያረጋጋ መሆኑን ገለጸ ።

የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ አባቡ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተመጣጣኝ ዋጋ እያከፋፈሉ ካሉት ውስጥ በሃያ ሚሊዮን ብር ወጪ ከአርሶ አደሮች የገዙት እህል ይገኝበታል።

እህሉን የሚያከፋፈሉት በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ አባላት፣ ለገጠርና ከተማ የሚኖሩ ጨምሮ 170ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች መሆኑብን ገልጸዋል።

ዩኒየኑ  በተጨማሪ የምግብ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ስኳርና ፣ ሣሙናና ሌሎት ሸቀጦችን ከፋብሪካና ዋና አከፋፋዮች እየገዛ  ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

በአካባቢው በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተፈጠረውን እጥረትና የዋጋ ንረት ከማረጋጋት ባሻገር ለዩኒየኑ መጠነኛ ትርፍ እንደሚያስገኝለትም አመልክተዋል።

ዩኒየኑ መቶ ኪሎ ጤፍ ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ብር፣ ስኳር በኪሎ ሀያ ሰባት ብር፣ በሃገር ወስጥ የተመረተ የኑግ ዘይት ሊትሩ  ሰማንያ ብር እየሸጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ነጋዴዎች ከሚያቀርቡት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ጤፍ የአንድ ሺህ  ብር፣ ስኳር የሃያ ብር እና ዘይት የሰላሳ ብር እና ሽንኩርት ደግሞ የአምስት ብር ቅናሽ አለው ብለዋል።

ፓስታ፣ ማኮሮኒ፣ ሳሙና፣ የግንባታ ቁሳቁሶች  መጠነኛ የአገልግሎት ጭማሪ በማድረግ በዞኑ ባቋቋማቸው ስልሳ  የመሸጫ ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ እየተከፋፈለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት የፍቼ ከተማ ነዋሪ አቶ ፉላሳ ለሚ በሰጡት አስተያየት ዩኒየኑ የሚያከናውነው የገበያ ማረጋጋት ስራ በተለይ ለመንግስት ሠራተኛውና  ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በእህል ጥራት ላይ የሚታየው ጉድለት ቢስተካከልና ህብረተሰቡ ተረጋግቶ የሚስተናገድበት ሁኔታ ቢመቻች የሚደግፉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሌላው የፍቼ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ስንቅነሸ አመንቴ በበኩላቸው  ዩኒየኑ  እህልና መሰረታዊ ሸቀጦችን በማቅረብ የሚያደርገው የገበያ ማረጋጋት ስራ ካልተገባ የነጋዴ ብዝበዛ እንደታደጋቸው ገልጸዋል።

ከዩኒየን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መልሰው የትርፍ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ነጋዴዎችን ብዝበዛ  በመለየት ሊያስተካክል እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ዩኒየኑ ከእህል ግዢና ሽያጭ በተጨማሪ ለአርሶ አደሮች የእርሻ ግብአትና መሰረታዊ ሸቀጦችን በማቅረብ የጀመረው ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የፍቼ  ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ  አቶ አዝመራው አደሬ ናቸው ። 

ለግንባታ አገልግሎት የሚውሉ ሲሚንቶ፣ ሚስማር እና ብረታ ብረት ከአምራቾችና አከፋፋዮች ዩኒየኑ እንዲያገኝ የገበያ ትስስር በመፍጠር የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት  አስተዳደሩ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዞኑ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ ዳምጤ ዩኒየኑ ለከተማና ገጠር ነዋሪዎች ለእርሻና ቤት ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ዕዎችን መሰረት አድርጎ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰጠው አገልግሎት መልካም   መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒየኑ የአካባቢውን የገበያ ፍላጎትና እጥረት መሰረት አድርጎ አገልግሎቱን በስፋት እንዲያቀርብ በጽህፈት ቤቱ በኩል ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አስራ ሰባት መሰረታዊ ማህበራትን በማቀፍ  በ1997ዓ.ም በ150ሺህ  ካፒታል የተቋቋመው  ዩኒየኑ  አሁን ላይ የማህበራቱን ብዛት ወደ 94 እና ካፒታሉን ደግሞ  ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ማድረሱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም