የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተቋሙ ሠራተኞች ያስገነባውን የህጻናት ማቆያ ማዕከል አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተቋሙ ሠራተኞች ያስገነባውን የህጻናት ማቆያ ማዕከል አስመረቀ

ጥር 18/2013 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተቋሙ ሠራተኞች ያስገነባውን የህጻናት ማቆያ ማዕከል አስመረቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተቋሙ ሠራተኞች ያስገነባውን የህጻናት ማቆያ ማዕከል ዛሬ አስመርቋል።
ማዕከሉ በ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን ከስድስት ወር እሰከ አራት ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ህጻናትን ለማቆየት የተሰራ ነው።
ማዕከሉን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ መርቀው ከፍተውታል።
ማዕከሉ ህፃናቱ እንደየ እድሜ ክልላቸው የሚቆዩበት አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ህፃናቱን በሞግዚትነት የሚያገለግሉ ባለሙያዎችም የተሟሉለት ስለመሆኑ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ የህጻናት ማቆያ ማዕከሉ እናቶች በቅርብ ሆነው ልጆቻቸውን እንዲያዩ በማድረግ በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ የህጻናት ማቆያ ማዕከሉ እናቶች ሊኖርባቸው የሚችለውን የአዕምሮ ጫና በማቃለል በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ገልፀው ሌሎች ተቋማትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተሚክሮ ሊጋሩ ይገባል ብለዋል።