በክልል የጤና ተቋማት በሚሰጥ ማሳወቂያ መሰረት የሚመዘገብ የልደትና ሞት ኩነት ምዝገባ አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

253

ጥር 18/2013 በክልሎች የጤና ተቋማት በሚሰጥ የማሳወቂያ ቅፅ መሰረት የሚመዘገብ የልደትና ሞት ኩነት ምዝገባ አነስተኛ መሆኑን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ። በክልሎች ማህበረሰብ አቀፍ የልደትና ሞት ኩነቶችን የማሳወቅ ስራ እንዳልተጀመረም አመልክቷል።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በየደረጃው ለሚገኙ ለጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች በማህበረሰብ አቀፍ የልደትና ሞት ማሳወቂያ ቅጽ አሞላልና አሰጣጥ ዙሪያ ያዘጋጀው የሁለት ቀን ስልጠና ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በ2009 ዓ.ም የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ መሰረት አንድ ሰው በጤና ተቋም ከተወለደ ተቋሙ አግባብነት ያላቸውን መረጃዎች የያዘ ማሳወቂያ ቅጽ ወዲያውኑ ሞልቶ ልደቱን ለማስመዘገብ ግዴታ ላለበት ሰው ማሳወቅ እንደሚገባው ይደነግጋል ብለዋል።

ከጤና ተቋም ውጪ የተወለደ ከሆነ በዝቅተኛው የአስተዳደር እርከን ላይ ያለው የጤና መዋቅር ወይም የጤና ባለሙያ አግባብ ያላቸውን ቅጾች በፍጥነት ሞልቶ ልደቱ ለተከሰተበት ቦታ ለሚገኘው የምዝገባ ጽህፈት ቤት ማሳወቅ አንዳለበትም አዋጁ እንደሚያስገድድ ገልጸዋል።

አዋጁ ለሞትም ተመሳሳይ የሆነ ግዴታ በጤና ተቋማት ላይ እንደሚያስቀምጥ አመልክተዋል።

ይሁንና ከክልሎች ተሞልተው በሚላኩ የምዝገባ ቅጂዎችና ከክልሎች በሚቀርቡ የምዝገባ አፈጻጸም ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከጤና ተቋማት በሚሰጥ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚመዘገብ የልደትና ሞት ኩነት ቁጥር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ነው አቶ ሙጂብ የጠቆሙት።

ከጤና ተቋማት ውጪ የቤት ለቤት ማህበረሰብ አቀፍ የልደትና ሞት ኩነቶችን የማሳወቅ ስራ እስካሁን እንዳልተጀመረም አመልክተዋል።

የጤና ተቋማት በጤና ጣቢያ የሚከሰቱ የልደትና የሞት ኩነቶችን በማሳወቂያ ወረቀት በመመዝገብ እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ የልደትና ሞት ኩነቶችን በማሳወቅ የምዝገባውን ሽፋን በማሳደግ የበኩላቸዉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ስልጠናውም ያለውን የአፈጻጸም መጠን ማሳደግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ እንደሆነም አክለዋል።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደሰላኝ ተሬሳ በበኩላቸው የልደትና ሞት ኩነት ምዝገባ አነስተኛ መሆን አንዱ ምክንያት የጤና ተቋማት የማሳወቂያ ቅጹን ሞልተው ማሳወቅ ላይ በሚፈለገው ደረጃ እየሰሩ ባለመሆኑ ነው ብለዋል።

በማህበረሰብ ደረጃ የልደትና ሞት ማስረጃውን ይዞ ለሚመለከተው አካል ከማሳወቅ አኳያ የግንዛቤ እጥረት እንዳለና በታችኛው የአስተዳደር እርከን ያሉ አመራሮች የወሳኝ ኩነት ምዘገባን እንደ ተጨማሪ ስራ የማየት መሆኑን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የአፈጻጸሙን ምጣኔ ለመጨመር ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እና ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ማህበረሰቡ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግና ኤጀንሲው እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ያለውን ተደራሽነት በማስፋት የምዝገባ ሽፋኑን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የስልጠና እና ስርጸት ዳይሬክተር አቶ ደበላ ጃለታ የልደትና ሞት ኩነት ምዝገባን ለማሳደግ ኤጀንሲው የጤና ተቋማትና አመራሮች ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጎልበት ይገባቸዋል ብለዋል።

የጤና ተቋማት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለምዝገባው ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የልደት፣ሞት፣ጋብቻ፣ጉዲፈቻና ፍቺ የምዝገባ ሽፋን መጠን 16 በመቶ መሆኑን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።