ከተማ አስተዳደሩ በመሬት ወረራ፣በባለቤት አልባ ህንጻዎች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አደረገ

103

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2013(ኢዜአ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ወረራ፣ በባለቤት አልባ ህንጻዎች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በቀበሌ ቤቶች ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አደረገ።

በጥናቱ መሰረትም 13 ሚሊዬን ካሬ ወይም 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በህገወጦች መያዙን ማረጋገጥ ተችሏል።

የተደረገውን ጥናት በማስመልከት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በሰጡት መግለጫ በመሬት ወረራ፣ በባለቤት አልባ ህንጻዎችና በጋራ መኖሪያና በቀበሌ ቤቶች ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እንደነበሩ አንስተዋል።

በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርና ቡድን በማዋቀር በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል።

በጥናቱ መሰረትም የመሬት ወረራን አስመልክቶ 13 ሚሊዮን ካሬ ወይም 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በህገ ወጦች መያዙን ገልጸዋል።

ወረራው በከተማዋ ካሉ 121 ወረዳዎች መካከል በ88 ወይም በ73 በመቶ በሚሆኑት ላይ ድርጊቱ መፈጸሙን ነው የገለጹት።

በከተማዋ በድምሩ 229 ሺህ 556 ካሬ ስፋት ያላቸው 332 ህንጻዎች ባለቤት የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባዋ ገለፃ ባለቤት አልባ ተብለው ከተለዩ ህንጻዎች መካከል 58ቱ ግንባታቸው ተጠናቀው ከ125 እስከ 409 ካሬ ላይ ተገንብተው ተከራይተው ይገኛሉ።

ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ እንዲሁም ባለቤታቸው ያልታወቁ 264 ህንጻዎች መኖራቸውም ይፋ ሆኗል።

በየካ 81፣ በላፍቶ ለቡ 73፣ ቦሌ፣ አቃቂ ኮልፌና ንፋስ ስልክ በአጠቃላይ 92 ህንጻዎች ሲኖሩ ቦሌ ወረዳ ስድስትና ሰባት 18 ህንጻዎች እንዳሉ ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋለ።

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ ደግሞ 21 ሺህ 695 ቤቶች በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 15 ሺህ 891 ምንም አይነት ህጋዊ መረጃ የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።

4 ሺህ 530 ባዶ ቤቶች መሆናቸውን ገልጸው 850 ቤቶች ደግሞ ለረጅም ጊዜ የተዘጉ ሲሆኑ በህገ ወጥ መልኩ በግለሰቦች የተያዙት ደግሞ 424 ቤቶች መኖራቸውን ጥናቱ አረጋግጧል።

በተጨማሪም በእጣ ሳይሆን በተለያዩ አግባቦች ለተጠቃሚዎች የተላለፉ 51 ሺህ 64 ቤቶች እንዳሉ ተደርሶበታል ነው የተባለው።

ሌላው በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግበው የሚገኘው ባለዕጣዎች የስም ዝርዝርና በመስክ ምልክታ የተገኘው የተጠቃሚዎች ስም ዝርዝር መሃከል ልዩነት ያላቸው ቤቶች 132 ሺህ 678 እንደሆኑና 18 ሺህ 423 ቤቶች የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው መሆኑን በጥናቱ ተለይቷል ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ 150 ሺህ 737 የቀበሌ መኖሪያና የንግድ ቤቶች አሉ።

ካሉት ውስጥ ተደራሽ የሆኑት 138 ሺህ 652 ሲሆኑ10 ሺህ 565 በቁልፍ ግዠ፣ሰብሮ በመግባት፣እና ሌሎች ህጉ በማይፈቅደው መንገድ መያዛቸውን አብራርተዋል።

7 ሺህ 723 ውል የሌላቸው፣ 2 ሺህ 207 ወደ ግል የዞሩ፣ 265 በ3ኛ ወገን የተያዙ፣164 የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሷቸው ያለቀቁ፣ 137 ተሽጠው ወደ ግል የተዘዋወሩ 1 ሺህ 243 ተዘግተው ወይም ታሽገው የተቀመጡ ናቸው።

5 ሺህ 43 የፈረሱና 180 አድራሻቸው የጠፉ ቤቶች መኖራቸውም በጥናት ማረጋገጥ ተችሏል።

በአጠቃላይ የንግድ የቀበሌ ቤቶች 25 ሺህ 96 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል በህገ ወጥ መንገድ የተያዙት 4 ሺህ 76 መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ጥናቱ በቤቶችና በመሬት ዙሪያ በህብረተሱቡ ዘንድ የሚስተዋለውን ብዠታ በማጥራት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

በጥናቱ ውጤት መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ለፖሊስና ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የጥናቱ ዝርዝር ውጤት ሪፖርት መደረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም