በዚህ አመት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ውክልና ለማሳደግ ከወዲሁ መስራት ይገባል- ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ

86

ጥር 18/2013 (ኢዜአ) በዚህ አመት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ውክልና ለማሳደግ ከወዲሁ መስራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ተናገሩ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራጭ ሴቶች ኮከስ ስብሰባ በላልይበላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤና የሴቶች ኮከስ የበላይ ጠባቂ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ሴቶች በፓርላማ ያላቸው ውክልና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። 

በዚህ አመት በሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተለያዩ ምክር ቤቶች ሴቶች ያላቸውን ውክልና ይበልጥ ለማሳደግ ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በፓርናማና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ሴቶችም ለተሻለ የስራ ተሳትፎና ጥንካሬ እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ፤ ኮከሱ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ሰብሳቢዋ ወይዘሮ አበባ ገዛኽኝ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የአቅም ግንባታ ስራ፣ የወንዶችን አጋርነት ማሳደግ፣ በተለያዩ አካቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ማድረግና ሌሎች ያከናወናቸውን ተግባራት ዘርዝረዋል።

በጎርፍ አደጋ ፣ በሃጫሉ ሁንዴሳ ሞትና በኮቪድ ምክንያት ከ65 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉ በሪፖርታቸው ተካቷል።

ውይይቱ ነገም የሚቀጥል ሲሆን በምርጫና የሴቶች ተሳትፎ ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

የሴቶች ኮከስ የፓርላማ ተመራጭ ሴቶች የተሰጣቸውን ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ መነሻ በማድረግ በሚወጡ ፖሊሲዎችና ህጎች ውሰጥ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና አቅማቸውን ለመገንባት የሚሰራ ነው።

የተመራጭ ሴቶችን አቅም በመገንባት በሚወጡ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና እቅዶች፣ የሴቶች ህገ-መንግስታዊ መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ የመታገል አላማም አለው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም