አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ከ8 ምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኖ ተለይቷል– ሚኒስቴሩ

391

አርባምንጭ ጥር 18/2013 (ኢዜአ) አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ከሚገኙ ስምንት ምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኖ መለየቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሰታወቀ።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 4ሺህ 858 ተማሪዎች ዛሬ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርና የእለቱ ክብር እንግዳ ዶክተር ሳሙኤል ሁርቃቶ እንደገለጹት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተልዕኮና በትኩረት መስክ በተደረገ ልየታ በሀገሪቱ ከሚገኙ ስምንት ምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኖ ተመርጧል።

ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ምርምር ለማካሄድና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሆነ ተናግረዋል።

“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግና አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው “ ብለዋል።

የኮቪድ- 19 ክስተት በዓለማችን ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ቀውስ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በቫይረሱ ክስተት ምክንያት በኢትዮጵያ በ2012 ትምህርት ዘመን 262 ሺህ 552 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም 275ሺህ 683 የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች ሳይመረቁ መቅረታቸውን አስታውሰዋል።

“የዛሬ ምሩቃን የቫይረሱን ተጽዕኖ ተቋቁማችሁ ለውጤት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት “ምሩቃን የነገዋን ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ወሳኞች በመሆናችሁ ባገኛችሁት ዕውቀት ያለምንም መድልዎ ህዝቡን ማገልገል አለባችሁ” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው “የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሀገሪቱን ብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ትምህርት ወሳኝ መሣሪያ ነው” ብለዋል፡፡

በ1979 ዓም በውሃ ቴክኖሎጂ ደረጃ ስራውን በመጀመር በ1996 ዓም ወደ ዩኒቨርሲቲ ያደገው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ 61 ሺህ 817 ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀዋል።

“በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ልዩነት ተከባብረው እንዲማሩ በመደረጉ ምሩቃን በፀረ-ሰላም ሃይሎች ተልዕኮ ሳይደናቀፍ ለዛሬው እለት በቅተዋል” ብለዋል ።

በዩኒቨርሲቲው ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ የተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ከዛሬዎቹ ምሩቃን መካከል የላቀ ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው የግብርና ምጣኔ ሀብት ተማሪ ተሜ አለኸኝ “በርትቼ በመስራት ላስመዘገብኩት ውጤት ስለተሰጠኝ ሽልማት ደስ ብሎኛል” ብሏል።

“ሁሉም ተመራቂ የመንግስትን ሥራ ብቻ መጠበቅ የለበትም” ያለው ተመራቂው በተማረበት የሙያ መስክ ሥራ በመፍጠር ሳይማር ያስተማረውን ህዝብ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።