በምዕራብ ሸዋ የሰሊጥ ልማት ለማስፋፋት አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ ነው- የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት

133

አምቦ/ሆሳእና ጥር 18 / 2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በአርሶ አደሩ ዘንድ እየተለመደ የመጣውን የሰሊጥ ልማት ለማስፋፋት አቅጣጫ ተይዞ እተየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ በ2012/13 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ከለማው ሰሊጥ 53 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱ ተነግሯል።

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሞያ አቶ ደጀኔ ገመቹ ለኢዜአ እንደገሉት ሰሊጥ በገበያ ላይ ካለው አዋጭነት የተነሳ በዞኑ አርሶ አደሮች ዘንድ በልማቱ የመሳተፍ ልምድ እየጎለበተ ነው።

የአርሶ አደሩን ሰሊጥ የማምረት ፍላጎት መሰረት በማድረግ ልማቱን ለማስፋፋት አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዞኑ በውስን አካባቢዎችና አርሶ አደሮች አማካኝነት ይካሄድ የነበረው የሰሊጥ ልማት አሁን ላይ በሰባት ወረዳዎች መስፋፋቱን ገልጸዋል ።

በአቡና ግንደበረት፣ አደአ በርጋ፣ አምቦ፣ ጮቢ፣ ሚዳቀኝ፣ ሜታ ሮቢና ኢሊፈታ ወረዳዎች ልማቱ የተስፋፋባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በ2012/13 ምርት ዘመን  መኸር ወቅት በወረዳዎቹ 6 ሺህ 99 ሄክታር ማሳ ላይ ከለማው ሰሊጥ 53 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል ።

እንደ ባለሞያው ገለጻ በምርት ወቀቱ የተገኘው የሰሊጥ ምርት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት 500 ኩንታል ብልጫ አለው ።

በዞኑ አሁን ላይ በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ አርሶ አደሮች ቁጥር 11 ሺህ መድረሱን የገለጹት ባለሞያው ልማቱን አመቺ ስነ ምዳር ባላቸው ሌሎች ወረዳዎች ለማስፋፋት አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የግብርና ምርምር ማዕከላት አዳዲስ የሰሊጥ ዝርያዎችን በማቅረብ ለአርሶ አደሮች እያደረጉ ባለው ድጋፍ ለሰብሉ ምርታማነት ማደግ አስተዋጾ ማድረጉንም ባለሞያው አስታውቀዋል።

በዞኑ የኢልፈታ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በሬቻ ፊጡማ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ከሚዘሩት ሰሊጥ አራት ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል።

በግብርና ባለሞያዎች በተደረገልኝ ምክርና ድጋፍ የሰሊጥ ምርቴ ጨምሯል" ያሉት አርሶ አደር በሬቻ ዘንድሮ ከተመሳሳይ ማሳ ላይ ከሰበሰቡት የሰሊጥ ሰብል ሰባት ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል ።

አርሶአደሩ እንዳሉት የሰሊጥ ምርት በገበያ ያለው ዋጋ ከሌሎች ሰብሎች የተሻለ በመሆኑ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል ።

”ከሌሎች የግብርና ስራዎች ጎን ለጎን በሰሊጥ ምርት ላይ በመሳተፍ ውጤታማ በመሆኔ ሌሎች አርሶ አደሮች በዘርፉ እንዲሳተፉ እያበረታታሁ ነው” ያሉት ደግሞ የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ተስፋዬ አለሙ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በሀዲያ ዞን ከመኸር እርሻ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የመምሪያው የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሳ ኤርቲሮ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ የተገኘው በ2012/13 ምርት ዘመን መኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 137 ሺህ ሄክታር ማሳ  ላይ ነው።

"በምርት ወቅቱ በኩታ ገጠም ማሳ የለማ ሰብል በኮምባይነር ታጭዶ በመወቃቱ ያጋጥም የነበረን የምርት ብክነት ለመቀነስ ተችሏል" ብለዋል ።

በምርት ወቅቱ ከተመረቱ ዋና ዋና ሰብሎች መካከል ስንዴ ፣ጤፍና በቆሎ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በምርት ወቅቱ የተገኘው የሰብል ምርት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት በ16 በመቶ እድገት አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም