የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሱሮ ቡርጎን ወረዳ ያስገነባው ትምህርት ቤት ተመረቀ

59

ዲላ፣ ጥር 18 ቀን 2013 (ኢዜአ) የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ሱሮ ቡርጎን ወረዳ ያስገነባው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመረቀ።

ለትምህርት ቤቱ ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገልጻል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንዳሉት፤ በምዕራብ ጉጂ ዞን ብቻ በመንግስትና ህብረተሰብ ተሳትፎ ደረጃቸውን የጠበቁ አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።

በክልሉ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነቡ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖራቸው አስታወቀዋል።

በተለይ ጽህፈት ቤቱ በአጭር ጊዜ በተሻለ ጥራት ገንብቶ የማጠናቀቅ ተሞክሮ ትምህርት የሚወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል።

"ትውልድን ማስተማር የአገራችንን የእድገት ጉዞ ለማፍጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው" ያሉት ደግሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ናቸው።

ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ ትምህርት ቤቱ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም