አዋጁ በመንግስት ተቋማት ወጥ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖርና የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ያደርጋል-ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

አዲስ አበባ ጥር 18/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ በመንግስት ተቋማት ወጥ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖርና የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ያደርጋል ሲል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገለጸ።

የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በሚል የፀደቀውን አዋጅ ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር በተዘጋጁ መመሪያዎች ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለመንግስት አስፈጻሚ አካላትና  ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት አመራሮች ገለጻ ተደርጓል።

የአስተዳደር ተቋማት በግለሰቦች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያደርጉት ጣልቅ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲቻል አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።

የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅሬታ ያለው ግለሰብ የውሳኔዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበትን ስርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህ ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑም እንዲሁ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሰለሞን አባይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ወጥነት ያለው የአስተዳደር ስነ-ሥርዓት አዋጅ አልነበራትም።

ይህም ግለሰብና ባለድርሻ አካላትን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች አተገባበሮች ላይ ችግሮች ይፈጠሩ እንደነበረ ገልጸዋል።

አዲሱ የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ወደ ተግባር ሲገባ ወጥ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ዕድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።

አዋጁ የአስተዳደር ተቋማት ሙያን መሰረት አድርገው እንዲሰሩ፣ ውጤታማነታቸው እንዲጨምርና ስራቸው ግልጽ፣ ሕጋዊና የተጠያቂነት መርህ ላይ እንዲመሰረትም ያደርጋል ብለዋል።

የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩና የሕግ የበላይነት፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማስቻል ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

አዋጁ በፌዴራል መንግስት ተቋማት መመሪያዎችና አስተዳደር እንዲሁም ለፌዴራሉ መንግስት ተጠሪ የሆኑ ከተማ አስተዳደሮች አስፈጻሚ አካላት መመሪያዎችና ውሳኔዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ መከላከያና የደህንነት ተቋማት ከዋና ሃላፊነታቸው በተጓዳኝ አገልግሎት መስጠትና የቁጥጥር ስራዎችን በሚመለከት በሚያወጧቸው መመሪያዎችና የአስተዳደር ውሳኔዎችም ላይ እንዲሁ።

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እንደገለጹትም አዋጁ የአስተዳደር ተቋማትን ውሳኔ የመስጠት ስልጣንና መመሪያ የማውጣት ውክልና በሕግ እንዲመራ የሚያደርግ ነው።

የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በአስተዳደር ተቋማት ያለአግባብ እንዳይሸራረፉና የተቋማት ስልጣንና ተግባር በፍርድ ቤቶች የክለሳ ስራ ሥርዓት ቁጥጥር እንዲደረግበትም ያስችላል ብለዋል።

በአዋጁ መሰረት ከዚህ በኋላ በተቋማት የሚወጡ መመሪያዎች ግልጽ፣ አሳታፊና አካታች በሆነ ሂደት እንዲወጡ ይደነግጋል ሲሉም ገልፀዋል።

አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የሚወስኑበትን ስርዓትና መርህ የሚደነግግ ሲሆን የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ቅሬታ የሚያስተናግዱበትን ስርዓት ማቋቋም እንዳለባቸውም ያስቀምጣል።

የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ የማርቀቅ ስራ በ2011 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን አዋጁ በ2012 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም