ሀንጋሪ በየዓመቱ ለ50 ኢትዮጵያዊያን ነጻ የትምህርት ዕድል እየሰጠች ነው

267

ጥር 18 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሀንጋሪ መንግስት በየዓመቱ ለ50 ኢትዮጵያዊያን የትምህርት ዕድል እየሰጠ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር አቲላ ኮፓኒ ገለጹ።

አውሮጳዊቷ አገር ሀንጋሪ እ.አ.አ 1962 ነበር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው።

በደርግ መንግስት ወቅት በኢትዮጵያና በሀንጋሪ መካከል የነበረው ግንኙነትና ትብብር ጠንካራ የነበረ ሲሆን የኢአዴግን መግባት ተከትሎ ግንኙነቱ ተቀዛቅዞ ኤምባሲዋን እስከ መዝጋት ደርሳ ነበር።

ሀንጋሪ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አድሳ ኤምባሲዋን እ.አ.አ 2016 ዳግም ስራ አስጀምራለች።ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮም ሀንጋሪ በኢትዮጵያ በኩል ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳለጥ እየተጠቀመችበት ነው።

በኢትዮጵያ የሃንጋሪ አምባሳደር አቲላ ኮፓኒ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ትብብር እንዳላት ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት በየዓመቱ ለ50 ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድልም አስገኝቷል።

በዚህም ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ጥናትና ምርምር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀንጋሪ ባለሀብቶች የሕክምና መሳሪያ በማምረትና በመሸጥ በዓለም ላይ ትልቅ ስም የገነቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ባለሀብቶቹ የሕክምና መሳሪያዎችን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች ከኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ጋር እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቅርቡም የሀንጋሪ መንግስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሚተዳደረው ምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታል ዘመናዊ የራጅ ማሽን ድጋፍ ማድረጉን አምባሳደር አቲላ ኮፓኒ ጠቅሰዋል።