በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲው በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የሰው ህይወት አለፈ

53

ድሬዳዋ፤ ጥር 18/2013(ኢዜአ) በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ትናንት እኩለ ቀን አካባቢ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት በአንድ ህንጻ ላይ የእሳት ቃጠሎ ደርሷል።

በአደጋው የአንድ ህጻን ህይወት ሲያልፍ በህንጻው ውስጥ የሚገኙ ክፍሎች፣ ፍራሾችና ሌሎች ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተጎራባች ከሆነው ገንደ ተስፋ ከሚባል አካባቢ ህጻናት ወደ ዩኒቨርሲው በአጥር ዘልለው በመግባት እንደሚጫወቱ አስታውሰዋል፡፡

እንደ ዶክተር ኡባህ ገለጻ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዲቪዥን ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረጉት ርብርብ እሳቱ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል፡፡

የደረሰው አደጋ በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖርም ተናግረዋል።

የአደጋውን መንስኤ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን ማጣራት መጀመሩን አመልክተው በዩኒቨርሲቲው የተዋቀረው ኮሚቴ የወደመውን ሃብትና ንብረት መጠን እየለየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም