ለወጣቶች የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሥልጠና ተጀመረ

871

አሶሳ /ጋምቤላ፤ ጥር 18/2013(ኢዜአ) ፡-ለወጣቶች የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሥልጠና በአሶሳ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ተጀመረ።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው ሥልጠና  ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ  እና ደቡብ ክልሎች የተውጣጡ  የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 350 በጎ ፈቃደኞች እየተሳተፉ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሠላም ግንባታና  ጸጥታ ቢሮ  ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ባደረጉት ንግግር በሥልጠናው በበጎ ፍቃድ ስራ ብሄራዊ መግባባት ይጠናከርበታል ብለዋል ።


የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በበኩላቸው ሥልጠናው እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው ሥልጠና ከተለያዩ የሀገሪቱ  አካባቢዎች የተውጣጡ 487 ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በሥልጠና መከፈቻ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንዳሉት በሀገሪቱ አሁን ለተገኘው ለውጥ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ይህንን ሃይል በሀገራዊ የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ውስጥ  ተሳትፎውን ለማጠናከር ሥልጠናው አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ለ45 ቀናት የሚቆየውሥልጠናውን ያዘጋጁት በሠላም ሚነስቴርና ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ትብብር ሲሆን በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ሥልጠናዎች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።

የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በቪዲዮ ኮንፍረንስ ለሠልጣኞቹ መልዕክት እንደሚያስተላልፉም ይጠበቃል።