ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር የምትደራደረው በቅድሚያ የሱዳን ኃይል የያዘውን መሬት ሲለቅ ነው- አምባሳደር ዲና

88

ጥር 18/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር የምትደራደረው የሱዳን ወታደራዊ ሃይል ድንበር ተሻግሮ የተቆጣጠረውን ግዛት ለቆ ሲወጣ በሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫቸው በብሔራዊ ጥቅም ጋር የተያያዙ ዲፕሎማሲያዊ አበይት ክንውኖች ላይ አተኩረዋል። 

ኢትዮጵያ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ሕግ ማስከበር ላይ በነበረችበት ወቅት የሱዳን ሃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር አልፎ የተቆጣጠረውን መሬት እንዲለቅ ኢትዮጵያ በትእግስት ስታሳስብ ስለመቆየቷ አንስተዋል።

የድንበሩን ጉዳይ እልባት ለመስጠት ከጦርነት ይልቅ ድርድርና ሰላማዊ ንግግር አሁንም ቢሆን በመፍትሔ አማራጭነት እንደምትቀበል ገልጸዋል።

ሁለቱን አገሮች ለመሸምግልና ለማደራደር የሚሹ ወገኖች ለጥረታቸው "እናመሰግናለን" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ኢትዮጵያ የምትደራደረው ግን የሱዳን ወታደራዊ ሃይል ከተቆጣጠረው መሬት በቅድሚያ ለቆ ከወጣ ነው ብለዋል።

የሱዳን ሃይል በሕገ ወጥ መንገድ የተቆጣጠረውን መሬት እንዲለቅ ቀደም ሲል የተጀመሩ የድንበር ኮሚሽን ቴክኒካል ቡድን ጥረቶች ቀጥለው የድንበር ጉዳይ እልባት እንዲሰጠው ጽኑ ፍላጎቷ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት የተጀመረውን ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ አቋም እንዳላት ተናግረዋል።

ከሳምንታት በኋላ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርነቱን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከደቡብ አፍሪካ የምትረከብ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ስለ ግድቡ የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ በዛሬው እለት ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ማቅናታቸውም የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ከደርግ ዘመን መንግስት በኋላ ተዘግቶ የነበረውን ኤምባሲዋን ዳግም በመክፈት ከኮንጎ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ፣ ለአፍሪካ አገሮች የነጻነት ተምሳሌት መሆኗን አስታውሰው

የአፍሪካ አገሮችም ለዚህ ትልቅ አክብሮት አላቸው ብለዋል።

በአንጻሩ በቀደምት የኢትዮጵያ መንግስታት የተሰሩ ውለታዎችን በማራከሳችን የሚሰጠንን አክብሮትና ውለታ ለዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ አልተጠቀምንበትም ሲሉም አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ቀደምት የነበራትን ተሰሚነትና ውለታ በመጠቀም ጭምር ዲፕሎማሲያዊ ስራዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን ትንኮሳ ያሳየችው ትዕግስትም ለሰላምና ዴሞክራሲ ያላትን አቅሟና ቁርጠኝነቷን የሚሳይ፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዘንድ ተዕጽኖ የሚያሳድር በዋጋ የማይገመት ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

በኢኮኖሚያዊ እና ዜጋ ተኮር ሳምንታዊ የዲፕሎማሲ ተግባራትን በተመለከተም አምባሳደሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ከነዚህም መካከል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከእንግሊዙ አቻቸው ዶሚኒክ ራብ ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

ከአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ስቴት ሴክሬታሪ ምክትል ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ጋርም በስልክ ውይይት ስለማድረጋቸው  አንስተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ህግ ማስከበር ተልዕኮ በኋላ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና መልሶ ማቋቋምና ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ለሁለቱ አገራት ተወካዮች ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በሱዳን ጉብኝት ለቆዩት የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ኢትዮጵያ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ መፍትሄ እንደምትሻ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩም ኢትዮጵያ የቀጣናው የሰላም መልህቅ በመሆኗ ለኢትዮጵያ ሰላምና ደህንንትን እንግሊዝ እንደምትደግፍ ስለመናገራቸው አንስተዋል።

በህዳሴ ግድብ ጉዳይም ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን መጉዳት እንደማትፈልግ ዋስትና መስጠቷን፣ ለዚህም የግድቡን መረጃና ደህነንነት ለሱዳን ስታስረዳ ስለመቆየቷ አንስውላቸዋል ነው ያሉት።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ረገድም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 27 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ስለማድረጋቸው፣ ራዚንግ ኢትዮጵያ በተባለው ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ዘመቻም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም