የህግ የበላይነትንና ሰብአዊ መብትን ለማስከበር የሚሊሻ አባላት ሚና የላቀ ነው- የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር

555

ፍቼ ጥር 17/2ዐ13 (ኢዜአ) የህግ የበላይነትንና ሰብአዊ መብትን በማስከበር ሂደት የአካባቢ ሚሊሻ አባላት ሚና የላቀ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ። 

ከዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች የተውጣጡ 11ሺህ 580 የአካባቢ ሚሊሻ አባላት  በደገም ወረዳ ለአንድ ወር የተሰጣቸውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ትናንት አጠናቀዋል።

የዞኑ አስተዳደር የፀጥታና ሰላም ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ በቀለ  በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጐለብት፣ የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና ሰብዓዊ መብት አንዲከበር ጥረት እየተደረገ ነው።

“በዚህ ሂደት ውስጥ የአካባቢ ሚሊሻ አባላት እየተጫወቱ ያለው  ሚና ከፍተኛ ነው ” ብለዋል።

“የዜጐችን መሰረታዊ መብቶች ለማስከበር ብዙ ውጣ ውረዶች ማለፍ ይጠይቃል” ያሉት ኃላፊው ለተግባራዊነቱ የአካባቢ ሚሊሻ አባላት በሃገሪቱ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ  ሊኖራቸው እንደሚገባ አመላክተዋል።

በዞኑ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ የፀጥታ አስከባሪዎች ወንጀልን ለመከላከልና የህግ የበላይነትን ለማስከበር  የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን ጠቅሰዋል።

የአካባቢ ሚሊሻ አባላት ችግሮች ከመስፋታቸው በፊት መረጃ በመስጠት፣ ቀላል ወንጀሎችን ደግሞ ለማረምና ለማስተካከል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት የአካባቢ ሚሊሻ አባላት ከምንጊዜውም በላይ የህብረተሰቡን ድጋፍና ትብብር የሚሹበት ጊዜ ነው” ያሉት ደግሞ የሂደቡ አቦቴ ወረዳ የፀጥታና የሰላም ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢጃራ ቱሉ ናቸው።

በወረዳው የህግ የበላይነትንና ሰብአዊ መብትን በማክበርና ማስከበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በየአካባቢው የሚታዩ ከባድ የነፍስ ግድያ፣ ዘረፋና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል የሚረዳ የግንዛቤ ስልጠና ለአባላት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የግራር ጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ሽመልስ ሃይሉ በበኩላቸው “የዜጐችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በማክበርና በማስከበር የህግ የበላይነት ላይ የማያወላውል አቋም ይዞ መንቀሳቀስ ይገባል” ብለዋል።

የወንጀለኞችን ተግባር ቀድሞ በመገንዘብ ወንጀልን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ኮማንደሩ አስታውቀዋል።

ለሚሊሻ አባላት የተሰጠው ስልጠናው ወታደራዊ ስልትን ጨምሮ በህገ-መንግስት፣ በሚሊሻ ደንብና መመሪያ፣ በሰላም አማካሪ ምክር ቤት አደረጃጀትና በሌሎች የሀገሪቱ ጉዳች ላይ ያተኮረ መሆኑ ታውቋል።