ኮሌጁን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው የለውጥ ትግበራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት

178

ጥር 17/2013 ( ኢዜአ) የብሔራዊ መረጃ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅን በኢንተለጀንስና በደህንነት መስኮች የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው የለውጥ ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በአገልገሎት መሥሪያ ቤቱ ሥር የሚገኘውን የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሥራ እንቅስቃሴን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።

አገልገሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በጉብኝታቸው ወቅት በሥልጠና ማዕከል ደረጃ የነበረው ተቋም ወደ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ደረጃ ማደጉ ከዚህ በላይ የመሥራት እምቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲ ኮሌጁን በአፍሪካ በኢንተለጀንስና በደህንነት መስኮች የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው የለውጥ ትግበራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተቋሙ አመራሮች ድጋፍ እንደማይለየውም አመልክተዋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማሲ መቀመጫ መሆኗን የጠቆሙት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ የብሔራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በዘርፉ የማሰልጠን አቅሙን ካሳደገ አፍሪካውያንን በማስልጠን የልህቅት ማዕከል መሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ፣ ለማዘመንና በቴክኖሎጂ ታግዞ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማስቻል አገልግሎቱ አስፈላጊውን የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፉን ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባለፈው ዓመት ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በደህንነት፣ በኢንተለጀንስ፣ በስትራቴጂክ ጥናትና በቋንቋ የትምህርት መስኮች በዲግሪና በዲፕሎማ ስልጠና ለመስጠት እውቅና ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም