ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር አሸነፈ

1671

ጥር 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆነ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በውድድሩ ጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተሳትፈዋል።

በጥሎ ማለፍ ውድድሩ ማጠናቀቂያ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደዋል።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በመርታት በአጠቃላይ ዘጠኝ ነጥብ በመሰብሰብ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

በተመሳሳይ ጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 አሸንፏል።

በአጠቃላይ ውጤት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ ጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በቅደም ተከተል ከሁለተኛ አስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የውድድሩ አሸናፊ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል።