የዩኒዬኑ አባላት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ

75

አሶሳ ጥር 17 / 2013(ኢዜአ) ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በአሶሳ ወረዳ የአንድነት ብድር እና ቁጠባ ዩኒዬን አባላት ጠየቁ፡፡

በዩኒዬኑ የስራ እንቅስቃሴ ላይ  በአሶሳ ተወያይተዋል፡፡

በ60 መሰረታዊ ማህበራት የታቀፉ  የዩኒዬኑ   አባላት መካከል አቶ ካሳሁን ገዛኸኝ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት የማህበራቱ አባላት በዩኒዬን ከታቀፉ በኋላ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ይሁንና ዩኒዬኑ ብድር በመስጠትም ሆነ በማስመለስ ረገድ የሚታዩበት ችግሮች እየጎሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አመራሮቹ  ችግሩን ለመፍታት ከመስራት ይልቅ ሃላፊነት ሲሸሹ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

አቶ ጸጋየ ገረመው በበኩላቸው ዩኒዬኑ ግዥ በሚፈጽምበት ወቅት መመሪያዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ  አስረድተዋል፡፡

ለረጅም ዓመታት ያልተመለሰ ብድር እንዳለ ጠቁመው ዩኒዬኑ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ስራዎችን ያለውል እንደሚፈጽም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የዩኒየኑ ገንዘብ እየባከነ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ብድር የራሳችሁ ገንዘብ ስለሆነ አትመልሱ በሚል ህብረተሰቡ ውስጥ አለአግባብ ቅስቀሳ በማካሄድ በዩኒየኑ አሠራር ላይ እንቅፋት እየተፈጠረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ መላኩ አስፋው ናቸው፡፡

በዩኒዬኑ ለብክነት የሚዳርጉ አሰራሮች እንዲወገዱ አደራጅ መስሪያ ቤቶች በተለይ የዩኒዬኑን መሠረታዊ ማህበራት አቅም ለማጠናከር ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የአሶሳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የዩኒዬኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሐብታሙ አያሌው በበኩላቸው ዩኒዬኑ ከአሠራር ውጪ ያለውል የሰጠው ብድር ገንዘብም ሆነ ያከናወነው ተግባር የለም ብለዋል፡፡

በዩኒዬኑ ጥቃቅን የአሰራር ክፍተቶች  እንደሚታዩ የገለጹት ሰብሳቢው ክፍተቶቹን ለማስተካከል እንደሚሠራም  ገልጸዋል፡፡

በተለይም አባላት ዩኒዬኑን በርቀት ብቻ ከመተቸት ይልቅ ቀርበው በመጠየቅ ለመፍትሔው በጋራ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አቶ ሐብታሙ አመልክተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ እና ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስካል አልቦሮ   መሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት የኦዲት ምርመራን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን በሚገባ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ምክንያቱ ኤጀንሲው በክልል ደረጃ ራሱን ችሎ ቢቋቋምም በዞን እና ወረዳ ግን በሌሎች መስሪያ ቤቶች ውስጥ እንደ አንድ መምሪያ መቀመጡ ነው ብለዋል፡፡

ችግሮቹ በዘላቂነት እንዲፈቱ ዩኒዬኖች ተቀናጅው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው በወረዳ እና ዞን የህብረት ሥራ ባለሙያዎች የሚገኙባቸው ተቋማት ማህበራትን መደገፍ እና መከታተል እንዳባቸው ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው በቀጣይ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመደጋገፍ ዩኒዬኖች እና ማህራት ያሉባቸውን ክፍተቶች ለማስተካከል እንደሚሠራ ወይዘሮ አስካል አስታውቀዋል፡፡

አንድነት የብድር እና ቁጠባ ህብረት ስራ ዩኒዬን በ2001 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በ60 መሰረታዊ ማህበራት የታቀፉ 10 ሺህ የሚጠጉ አባላት እና ከ17 ሚሊዮን  800ሺህ  ብር በላይ ካፒታል እንዳለው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

አንድነትን ጨምሮ  በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 108ሺህ 716 አባላትና ከ347 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው  23 ዩኒዬኖችና 1ሺህ545 የህብረት ስራ ማህበራት እንደሚገኙ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም