የኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች በጋራ ወሰኖች አካባቢ ልማትን ለማሳለጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

87

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/2013 ( ኢዜአ) የኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች በጋራ ወሰኖች አካባቢ ያለውን ልማትን ማሳለጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የኦሮሚያና የሱማሌ ክልሎች የሰላምና የልማት የጋራ መድረክ ከፌዴራል መንግስት የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና የየክልሎቹ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ክልሎቹ በጋራ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን የተመለከተ የአምስት ዓመት ዕቅድ ቀርቧል።

በእቅዱ እንደተመለከተው ወደ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚዋሰኑት የሁለቱ ክልል ነዋሪዎች በርካታ ነገሮችን ይጋራሉ።

በ12 ዞኖች እና በ48 ወረዳዎች በቋንቋ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ተቆራኝተው እንደሚኖሩ ነው የተገለጸው።

በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ያለውን አብሮነት ማጠናከር፣ የግጭት አፈታት ውይም የሰላም ግንባታ፣ መሰረተ ልማት ዝርጋታና የፕሮግራም አመራርን ለማጠናከር ታቅዷል።

ለእነዚህ ስራዎች ማስፈጸሚያም ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘ ሲሆን ሁለቱ ክልሎች በጋራ ከሚያዋጡት እንደሚሸፈንም ተመላክቷል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በወሰን አካባቢዎች ግጭቶችን ማስቀረትና አብሮ መልማት ላይ በስፋት ተሰርቷል።

"በቀጣይ ከግጦሽ፣ ከውሃና ከሌሎች የጋራ ሀብቶች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶችን ለመቅረፍ ጠንካራ የልማት ሥራዎች ይሰራሉ" ብለዋል።

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ፤ የልማት ሥራውን በጋራ ለማከናወን ክልሉ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በእስካሁኑ እንቅስቃሴ የተገኙ መልካም ተሞክሮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የሥራ ኃላፊዎችም የትብብር መድረኩ የሚደገፍና ጠንክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ደግሞ አካባቢዎቹ የአርብቶ አደር አካባቢዎች እንደ መሆናቸው ከውሃ አቅርቦት ጋር የሚያያዙ ችግሮች ትልቅ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ነው የገለጹት።

ክልሎቹ እያደረጉ ያሉት ተግባር ለኢትዮጵያ ሰላም ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው።

የጋራ መድረኩ የፖለቲካ ፍላጎትና ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ጠቁመው፣ ዘላቂ የመሆን እድሉም ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ሁነቱ ለሌሎች ክልሎች ትልቅ ምሳሌ ይሆናል" ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ፣ ሚኒስቴሩም በቅርበት እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ በሁለቱም ክልሎች የሥራ ቋንቋዎች ማስተማር መጀመራቸውም መልካም ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም