የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ሚናቸውን ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው-ኤጀንሲው

95

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/2013 ( ኢዜአ)  የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ኤጀንሲው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደ አዲስ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን  ለኢዜአ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውንም ነው የገለጹት።

ከዚህ ቀደም በመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጥርጣሬ ሲተያዩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በተከናወነው የሪፎርም ስራም ይህ እንዲቀረፍ ተደርጓል ብለዋል።

አሁን ላይ በመንግስትና በድርጅቶቹ መካከል ገንቢና መተማማን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፈጠሩንም አንስተዋል።

በመሆኑም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአዋጅ በተቀመጠው መሰረት በምርጫ ሂደት ላይ የሚሳተፉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም አቶ ፋሲካው ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የአገር ውስጥ ድርጅቶች በመራጮች ምዝገባና ትምህርት እንዲሁም ምርጫን መታዘብ የሚችሉበት ስርዓት መኖሩንም ገልጸዋል።

ይህን ለማድረግም ከኤጀንሲው በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እነዚህን ሂደቶች በማሟላት መጪው አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃና ሰላማዊ  እንዲሆን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም  አመልክተዋል።

ድርጅቶቹ ለዴሞክራሲ መጎልበት ባላቸው ሚናና ከተቋቋሙለት ዓላማ አኳያ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በግንቦት ወር መጨረሻ እንደሚካሄድ ይፋ ማደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም