የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮሮናን በመከላከል ምርት እንዳይስተጓጎል ያደረገው ጥረት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ...ቋሚ ኮሚቴ

108

ሀዋሳ፤ጥር 17/2013 (ኢዜአ) የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮሮናን በመከላከል የምርት ሂደቱ እንዳይስተጓጎል እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎችም ተቋማት ምሳሌ እንደሚሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ። 

የኮሚቴው አባላት ፓርኩን በጎበኙበት ወቅት ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ከበደ እንዳሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው የተቋቋሙት የሥራ ዕድል ፈጠራን ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ  ነው።

በዚህ ረገድ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ መሆኑን ባደረጉት ቅኝት ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ ኮሮናን መከላከል መሠረት ባደረገ መልኩ በውስጡ ያሉ ኩባንያዎች ሳይዘጉ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የከፋ ጫና ውስጥ እንዳይገባ ያደረገው ጥረት ውጠታማ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ተግባሩ ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን ገልፀው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማስገንዘብ፤ ፓርኩ ከአካባቢው ማህበረሰብና የመንግስት አካላት ጋር ያለውን ቅንጅትም ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

በኩባንያዎች ውስጥ የተቀጠሩ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ እንደሆነ መረዳታቸው የገለጹት አቶ ዘውዱ በጊዜ ሂደት ማሻሻያዎች በማድረግ የሚስተካከል እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሠራተኛው ደመወዝ ከፍ በማድረግ መደገፍ ባይቻልም በተለይ የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ማቃለል እንደሚቻልና ኢንዱስትሪ ፓርኩም በዚህ ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅት ገልጸዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ በበኩላቸው ፓርኩ ተቆጥሮ የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ከ28 ሺህ ባለይ ሠራተኞች እንዳሉ ጠቁመው፤ኩባንያዎች ውስጥ በሚሰሩበት ወቅት የተሟላ የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲቀስሙ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

ፓርኩ ኮሮናን በመከላከል ሥራው እንዲቀጥል ለማድረግ ለፓርኩ ማህበረሰብ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ገልፀው፤ በሥራ ወቅት መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች እንዲደረጉም ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

የሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት  አቶ ፍፁም፤ በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎች ቦታ ተሰጥቷቸው ሠራተኞቻቸው ቤት እንዲገነቡ በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የቤት መስሪያ ቦታ ያላቸው በፓርኩ አቅራቢያ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ከባንክ ብድር አግኝተው ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶችን በመገንባት ችግሩን ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሲዳማ ክልል የሚገኙ የዘርፉን ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች በመቃኘት ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም