ምክር ቤቱ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በአገሪቱ ለማዳረስ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዲታረም አሳሰበ

81

አዲስ አበባ፣ ጥር 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) የውሃ ልማት ኮሚሽን በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በመላ አገሪቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የያዘውን እቅድ ለማሳካት በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች በማስተካከል መስራትን እንደሚጠይቅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑትን የውሃ ልማት ኮሚሽን፣ የመስኖ ልማት ኮሚሽንና ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን የስድስት ወር አፈፃፀምን ገምግሞ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

የውሃ ልማት ኮሚሽን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሰራው ስራ መልካም ተብሏል።

ኮሚሽኑ ከሌሎች ጋር በመቀናጀት በመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን ሃይጂንና ቁሳቁስ በኩል ያከናወናቸውን ተግባራት ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል።

የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በግማሽ አመቱ በ32 ከተሞች ዘመናዊ የውሃ አገልግሎት የአሰራር ዝርጋታ ክንውኑንም እንዲሁ።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ለክልሎችና ከተሞች የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ደካማ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲሃ የሱፍ የኮሚሽኑ የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ እቅድ አፈፃፀም ዝቅተኛ በመሆኑ ቀጣይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን አሁን ካለበት 55 በመቶ ወደ 100 በመቶ ለማድረስ ለተያዘው እቅድ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች በማስተካከል መስራትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በግዥና በሰው ሃይል ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለውን ችግርም በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የሳኒቴሽን የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ግንባታ አፈፃፀምም ዝቅተኛ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ነው ያሉት።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በሰጡት ማብራሪያ የፕሮጀክቶች ስራ ላይ ድጋፍና ክትትሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የውሃ ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሸዋነሽ ደመቀ በበኩላቸው አቅም ያለው ተጫራች ባለመገኘቱ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄዱ ማድረጉን አስረድተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦችና ማስተካከያዎች ኮሚሽኑ ተቀብሎ እንደሚያስተካክልም አረጋግጠዋል።

የመስኖ ልማት ኮሚሽን የፕሮጀክቶች አፈፃፀም አነስተኛ በመሆኑም በትኩረት እንዲሰራ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የመገጭ፣ የአርጆ ደዴሳ፣ የዛሪማና ሌሎች ግድቦች አፈፃፀም አነስተኛ መሆኑንም በማሳያነት ተጠቅሷል።

ኮሚሽኑም በሰጠው ምላሽ በተለይም የሲሚንቶ እጥረት ለፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት መሆኑን ጠቅሶ፤ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም