የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለልተኛ አማካሪ ቡድን ተመሰረተ

389

ሆሳዕና፤ጥር 17/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ወንጀልን በህብረተሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ ለመከላከል የሚያግዝ የፖሊስ ኮሚሽን ገለልተኛ አማካሪ ቡድን ዛሬ ተመሰረተ።

በሆሳዕና ከተማ በተዘጋጀው መድረክ የተመሰረተው  ገለልተኛ  አማካሪ ቡድን  ከክልሉ  በየደረጃው የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣   ሀገር ሽማግሌዎች፣ የእድር መሪዎች፣   ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአባልነት ያቀፈ ነው።

በመድረኩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ እንዳሉት ህዝቡ ለሠላምና  ፀጥታ  ሥራ ስኬታማነት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ለማጠናከርና የፖሊስን አገልግሎት  ለማዘመን ገለልተኛ የአማካሪ ቡድን መመስረት አስፈልጓል።

በተለይ በየደረጃው ፖሊሲያዊ ስራን በቅርበት የሚያማክር ና የሚደግፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን መደራጀቱ ቀልጣፋና ብቃት ያለው የፖሊስ  ተቋም ለመገንባት  እየተደረገ  ያለውን   እንቅስቃሴ ለማጎልበትይረዳል ብለዋል።

የአማካሪ ቡድን አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣትለክልሉ  ዘላቂ  ሠላምና ፍትህ መስፈን እንዲተጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከልና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ቡድን  መሪ ኮማንደር ሲሳይ ዳካ በበኩላቸው በህብረተሰቡ የተመረጡ ገለልተኛ የአማካሪ ቡድን መመስረቱ ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር የህዝቡን ሠላምና ደህንነት በዘላቂነት  ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የወንጀል መከላከል ስራን በማከናወን ውጤታማ  አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

የአማካሪ ቡድኑ አባል ቀሲስ ልሳነወርቅ ሹምዬ በሰጡት አስተያየት የሠላም  ባለቤት  የሆነው ህብረተሰብ የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ  የሚያደርገውን  ተሳትፎ  ለማጠናከር  የቡድኑ መመስረት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

 ሀገራዊ ሠላም የሚረጋገጠው ሁሉም አካባቢውን ነቅቶ ሲጠብቅ ነው ያሉት አስተያየት  ሰጪው፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ሠላሟ የሠፈነባት ሀገርን ለመፍጠር  የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ  የሀገር ሽማግሌ አቶ ቦጋለ ቦንታ በበኩላቸው  የአማካሪ ቡድኑ  መመስረት  ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል  ከፍተኛ  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

23 አባላት ያሉት የገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ዋና ሰብሳቢ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሲሆኑ ምክትል ሰብሳቢ ደግሞ አቶ ብርሃኑ ኃይሌ  ሆነው ተሰይመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም