"የአሜሪካ ድጋፍ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት ዕድሎች እንዲስፋፉ አድርጓል" - አምባሳደር ማይክል ራይነር

70

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/2013 ( ኢዜአ) በአሜሪካ ድጋፍ "የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት እድሎች እንዲስፋፉ በተለይም አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን እንዲያጎለብቱ ተደርጓል" ሲሉ አምባሳደር ማይክል ራይነር ተናገሩ። 

ተሰናባቹ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር አገራቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓን ገልፀዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩባቸውን ያለፉት ሦስት ዓመታት ቆይታቸውን አስመልክተው ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር ተወያይተዋል።

አሜሪካ ለተለያዩ ዘርፎች ፈሰስ ባደረገችው በዚህ ገንዘብ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት ዕድሎች መስፋፋታቸውንና አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን እንዲያጎለብቱ መደረጉን ተናግረዋል።

ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑና በርካታ የአሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ተዋናዮች ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ድጋፉ እገዛ ማድረጉንም ነው ተሰናባቹ አምባሳደር የገለፁት።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል ለምታደርገው ጥረት አሜሪካ ድጋፍ ያደረገች ሲሆን በተፈጥሯዊ ችግር ሠብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው ዜጎችም ድጎማ ተደርጓል።

የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ ለማዘመንና የጤና ዘርፉን ዕድገት በተለይም የኮቪድ-19 ጫናን ለመቋቋምም ድጋፉ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ያካሄዷቸውን ዘርፉ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች መደገፏን ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

በዚህ ዘርፍ ድጋፍ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሃሳቦች ከአሜሪካ የዴሞክራሲ መርህና እሳቤ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ እንደሆነም አስረድተዋል።  

"ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት እንዲሰፋ ተደርጓል" ነው ያሉት አምባሳደር ማይክል ራይነር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ያከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች ተቋማዊ እንዲሆኑና የሚፈለገውን ግብ እንዲመቱ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም ምከረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

"ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የነበሩ ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶች፣ አሜሪካ ድጋፍ መሠረዟና የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጣዊ ሁኔታ መጠመድ ግንኙነቱ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል" ብለዋል።

ያም ሆኖ በቀጣይ ተሹሞ የሚመጣው የአሜሪካ አምባሳደር የአገራቱ ግንኙነት ላይ ይበልጥ መሥራት እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሠላም ማስከበርና በቀጣናው ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት።

አምባሳደሩ "በኢትዮጵያ በቆየሁባቸው ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አዎንታዊ ውጤት መገኘቱን አምናለሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከ100 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም