ገበያ ላይ ከዋሉ 36 የእንስሳት መድሃኒቶች ዓይነቶች 10ሩ ከደረጃ በታች ሆነው ተገኝተዋል

1529

ጥር 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ገበያ ላይ ከዋሉ 36 የእንስሳት መድሃኒቶች ዓይነቶች ላይ በተደረገ የላቦራቶሪ ፍተሻ 10ሩ ከደረጃ በታች ሆነው መገኘታቸውን የእንስሳት፣ መድሃኒትና መኖ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የእንስሳት መኖና መድሃኒት ቁጥጥር ስራ መጠናከር እንዳለበት አሳስቧል።

ባለስልጣኑ የሁለተኛው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቦ በተደረገ ውይይት የእንስሳት መኖና መድሃኒት ጥራት ወሳኝ መሆኑ ተነስቷል።

የእንስሳት መኖና መድሃኒቶችን ማቅረብ ላይ ተሰማርተው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ አካላት አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠይቋል።

ጥራት የጎደላቸው መድሃኒቶችን ከገበያ መሰብሰብና ከውጭ የሚገቡትም ደረጃቸውን ስለመጠበቃቸው ተገቢው ቁጥጥር መካሄድ እንደሚኖርበትም ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጠርዙ ዳያ የእንስሳት መድሃኒቶች ተፈላጊውን ደረጃ ስለማሟላታቸው የላቦራቶሪ ፍተሻ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልፀው፤ ከውጭ ገብተው ፍተሻ ከተደረገባቸው 24 መድሃኒቶች መካከል 22ቱ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

“ገበያ ላይ በዋሉ 36 መድሃኒቶች ላይ በተደረገ የላቦራቶሪ ፍተሻ 10ሩ ከደረጃ በታች ሆነው ተገኝተዋል” ብለዋል።

በሌላ በኩል ከደረጃ በታች የሆነ የእንስሳት መኖ አቅራቢ ድርጅት በተደጋጋሚ ማስተካከያ እንዲያደርግ ቢነገረውም ባለማሻሻሉ እርምጃ እንደተወሰደበት ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ጠርዙ ገለጻ፤ መድሃኒቶች ገበያ ላይ ከዋሉ በኋላ መሰብሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ የኬላ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ተደርጓል።

ከውጭ አገሮች የገቡ ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድሃኒቶች እንዲመለሱ መደረጉም ተገልጿል።

በቀጣይ ሕገ-ወጥ የመድሃኒት ስርጭት ያለበትን ደረጃ በጥናት ለመለየትና የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጥናት መካሄድ እንዳለበት የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች ተናግረዋል።

ለዚህም 14 የመድሃኒት መሸጫ ቦታዎች መለየታቸውን ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ ባለሥልጣኑ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገቡና በገበያ ላይ የዋሉ የእንስሳት መድሃኒቶችና መኖ ቁጥጥር ስራውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

ደረጃቸውን ያልጠበቁ የእንስሳ መድሃኒቶችና መኖ አቅርቦት ላይ ተሳትፈው በተገኙ አካላት ላይ አስተማሪ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ላይ ያለው ክፍተት መታረም እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል።