የደቡብ ክልል መንግስትና የዩኒቨርሲቲዎች የትብብር ፎረም ተመሰረተ

58

ሶዶ፣ ጥር 17/2013 (ኢዜአ)- በደቡብ ክልል መንግስትና በክልሉ በሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል የትብብር ፎረም ዛሬ ተመሰረተ።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የፎረም ምስረታ ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት"የሀገር ልማትና ዕድገትን ለማፋጠንና የሀብት ብክነትን ለመቀነስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ የምርምር ስራዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል" ብለዋል።

መንግስት ለያዛቸው ልማትና ዕድገት ውጥኖች ስኬታማነት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራና በትብብር መንፈስ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥምረት መመስረቱ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ አመላክተዋል።

የፎረሙ መመስረት የክልሉ መንግስት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለሚያከናውናቸው ተግባራት የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው "መንግስት ያለመውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር መስራት ይገባል" ብለዋል።

ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርዓት በመዘርጋት የህዝቦችን ዘላቂ ሰላምና ተጠቃሚነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ለተግባራዊነቱም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

"የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቀጣይ አስር ዓመት የትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ተልዕኳቸውን ለማሳካት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙበት አካባቢን ማህበረሰብ ለማገልገል ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በፎረም ምስረታ ስነ ስርአት ላይ በክልሉ የሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮችና የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም