በአፋር ክልል የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው- አቶ አወል አርባ

100

ሠመራ ፤ ጥር 17/2013(ኢዜአ) በአፋር ክልል የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ። 

የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎችና ባለሀብቶች የተሳተፉበት ክልል አቀፍ የምክክር  መድረክ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተጀምሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመድረኩ  እንደተናገሩት የተጀመረው ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞም ሆነ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት  እንዲሁም እያደገ የመጣውን ሰፊ የስራ እድል ጥያቄ ለመመለስ ኢንቨስትመንት ወሳኝ ነው።

ለዚህም እውን መሆን  ያሉንን ሰፊ ለም መሬትና ተያያዥ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎች ከማውራት ባለፈ ወደ ተጨባጭ ሃብት መቀየር ይኖርብናል ብለዋል።

ከዚህ በፊት በመንግስትና ባለሀብቶች መካከል የነበረውን ያለመተማመንና በጥርጣሬ የመተያየት የአመለካከት ችግርች በማቃለል ተቀራርበው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረገው ጥረትም በክልሉ በግብርና እና የማዕድን ዘርፍ  ልማቶች የሀገር ውስጥና ውጭ ባለሃብቶች እየተሳተፉ  እንደሚገኙ አቶ አወል አስረድተዋል።


ሆኖም  ክልል ካለው  ሰፊ ለም-መሬት፣ የተፈጥሮ ሃብትና ለወደብ ካለው ቅርበት አንጻር ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት ገና ብዙ ስራዎች ስለሚቀሩ ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት፣ ባለሃብቶችና ህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


ባለሃብቶች ውጤታማ  እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ብለዋል።


ከዚህ አኳያ መድረኩ በክልሉ ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችን ለይቶ በማወቅ በዘርፉ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችና ማነቆዎችን  በመለየት ፈጣን  እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።


በመድረኩ የተገኙት የፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር  ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው በአፋር ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት በአግባቡ ከለማ ከክልሉ  አልፎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊደግፍ የሚችል ነው ብለዋል።


በክልሉ የተጀመሩ የማዕድን ሃብት ልማትና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲያድጉ ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርበው  እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።


የክልሉ መንግስትም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የመስሪያ ቦት አቅርቦት ጨምሮ እያደረጋቸው ያሉት የድጋፍና ክትትል ስራዎች የሚበረታቱና በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።


ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ  ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አስፈጻሚ አካላትና ባለሀብቶች  እየተሳተፉ መሆኑን ሪፖርተራችን ከሠመራ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም